Fana: At a Speed of Life!

ከ5 እስከ 10 በመቶ ያህሉ የዓለም ሕዝብ በድብርት ይጠቃል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ድብርት ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በእጥፍ የሚከሰት የአዕምሮ ህመም ነው፡፡

አንድ ሰው የድብርት ህመም አለበት ለማለት ምልክቶቹ ለሁለት ሣምንት እና ከዚያ በላይ በተከታታይ መታየት ይኖርባቸዋል፡፡

ድብርት በተለይ በጉርምስና እና በ40ዎቹ መጨረሻ የዕድሜ ክልል በሥፋት የሚስተዋል ሲሆን፥ በጊዜ ካልታከመ ሕይወትን እስከማሳጣት የሚደርስ የአዕምሮ ጤና ችግር መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ሕመሙ ሥር እየሠደደ ሲመጣም ተጠቂዎቹን መኖር እስከ ማስጠላት ፣ ኑሮን የመቋቋም አቅም እስከ ማሳጣት እና እራስን ለማጥፋት እስከ መነሳሳት ያደርሳል፡፡

ድብርት ካለባቸው ሰዎች መካከል 15 በመቶ ያህሉ እራሳቸውን እንደሚያጠፉም ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

በዓለምአቀፍ ደረጃ በዓመት እራሳቸውን ከሚያጠፉ ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች÷ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ7 እስከ 8 ሺህ ያህል ሰዎች አብዛኞቹ በድብርት የተጠቁ ስለመሆናቸውም ይነሳል፡፡

ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለባቸውም በጥናት ተረጋግጧል፡፡

በአጠቃላይ የድብርት ዓይነቶች በርካታ ቢሆኑም÷ ቀላል፣ መካከለኛ እና ከባድ ተብለው ይከፈላሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት እና ከሱስና ተያያዥ ችግሮች ጋር በተያያዘ ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ስለ ድብርት መንስዔ፣ ምልክቶች፣ ጉዳት እና ሕክምና ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ድብርት ምንድን ነው? ምልክቶቹስ?

የድብርት (ዲፕሬሽን) ሕመም በሰፊው ከሚታዩ የአዕምሮ ጤና ችግሮች አንዱ ሲሆን÷ የስሜት መውረድን ብሎም የደስታ ስሜት ማጣትን ያሳያል ይላሉ፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ አንድ ሰው በድብርት ውስጥ ሲሆን በውስጣዊ ስሜቱ እና በውጫዊ ገጽታው እንደሚንጸባረቁ ጠቅሰው ÷ ይህም ደስታ ማጣት፣ መከፋት፣ ጥልቅ በሆነ ሀዘን ውስጥ መሆን ናቸው፡፡

ድብርት የስሜት በሽታ በመሆኑ ከስሜት መቃወስ ጋር ተያይዞ የሐሳብ መዛባት ያስከትላል ብለዋል፡፡

በዚህም ሰዎች ለእራሳቸው፣ ለሕይወት እና ለቀጣይ ኑሯቸው ያላቸው አመለካከት ጨለምተኛ የመሆን አዝማሚያ ይታይበታልም ነው የሚሉት።

ከድብርት መገለጫዎች መካከል÷ የስሜት መዛባት፣ በፊት ያስደስቱ በነበሩ ሁኔታዎች አለመደሰትና አለመፈለግ፣ የአስተሳሰብ (የአዕምሮ እና የአካል) ፍጥነት መቀነስ (ዘገምተኝነት)፣ የምግብ ፍላጎት እና ክብደት መቀነስ ይጠቀሳሉ፡፡

በአንጻሩ በአንዳድ ሰዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የምግብ ፍላጎት መጨመር፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ምክንያቱ በግልጽ ያልታወቀ ከፍተኛ ድካም፣ እራስን በከፍተኛ ሁኔታ አሳንሶ ማየት፣ እራስን በከፍተኛ ሁኔታ መውቀስ (የተጋነነ የጥፋተኝት ስሜት)፣ የኃጢያተኝነት ስሜት፣ ሕይወትንና ኑሮን መጥላት፣ ሞትን መመኘት፣ እራስን ለማጥፋት ማሰብ ብሎም ለማጥፋት መሞከር የድብርት መገለጫዎች ናቸው፡፡

የድብርት መንስኤ ይታወቃል?

ድብርት ብዙ ጊዜ እንደማንኛውም የአዕምሮ ህመም ቁርጥ ያለ መንስኤ ባይኖረውም ÷ የታወቁ ሥነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና አካላዊ አጋላጭ ሁኔታዎች አሉት ይላሉ ባለሙያው፡፡

ጾታዊ ጥቃት፣ ድንገተኛ የኢኮኖሚ ክስረት፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋን ተከትሎ የሚፈጠር ማህበራዊ መቃወስ፣ በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙ ከፍተኛ ጫናዎች እና ከሥራ መፈናቀል ለድብርት አጋላጭ የሚባሉ ማህበራዊ ችግሮች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ከሥነ-ልቦናዊ ችግሮች መካከል የአዕምሮ ጥቃት ለድብርት አጋላጭ መሆኑ ሲጠቀስ÷ አንዳንድ መድኃኒቶች፣ አደንዛዥ እና አነቃቂ ዕጾች እና ሥር የሰደዱ አካላዊ (ሥነ ሕይወታዊ) ህመሞች በድብርት አጋላጭነታቸው ይነሳሉ፡፡

ድብርት በዘር የመተላለፍ ባህሪ ስላለው በቤተሰባቸው የድብርት ህመም ታሪክ ያላቸው ሰዎች ለድብርት የመጋለጥ ዕድላቸው እንደሚጨምር ተገልጿል፡፡

ድብርት በሁሉም የዕድሜ ደረጃ ሊታይ እንደሚችል ቢታመንም በተለይ በጉርምስና እና በ40ዎቹ መጨረሻ የዕድሜ ክልል ላይ በጉልህ ይታያል፡፡

ድብርት ሕክምና አለው ?

ድብርት እንደ ሕመሙ ዓይነትና ክብደት በምርመራ ተለይቶ ሥነ-ልቦናዊ (ሳይኮ ቴራፒ) እና የመድኃኒት ሕክምና ይሰጣል፡፡

የድብርቱ ዓይነት ቀላል ከሆነ ሥነ-ልቦናዊ ሕክምና፣ ከባድ ከሆነ ደግሞ የመድኃኒት ሕክምና ይሰጣል ነው የሚሉት፡፡

በተጨማሪም የሕመሙ ተጠቂዎች ሆስፒታል ተኝተው ሊታከሙ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

ሕመሙ ሥር ሰዶ ምግብ መመገብ ፣ መናገር ብሎም መድኃኒት ለመውሰድ ፈቃደኛ የማይሆኑበት ጊዜ ከደረሰ አንጎልን በኤሌክትሪክ የማነቃቃት ሕክምና ሊሰጥ ይችላልም ብለዋል፡፡

ድብርት ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በእጥፍ ጨምሮ የሚታይበት ሁኔታ በግልፅ ባይታወቅም መላ-ምቶች እንዳሉ ግን ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ያስቀምጣሉ፡፡

በሴቶች ላይ በተፈጥሮ በተለያዩ ሁኔታዎች የሚቀያየሩ የሆርሞን ልዩነቶች (ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት ድብርት)፣ እንዲሁም በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያሉ የተፈጥሮ ቅመሞችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከሥነ-ልቦና አንጻርም ሴቶች ለድብርት የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ያነሳሉ፤ ለምሳሌ ተገዳ የተደፈረች ሴት ለድብርት የመጋለጥ ዕድሏ ሠፊ ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ።

በተመሳሳይ ሴቶች ላይ የቤት ውስጥ ጥቃት መበራከቱ፣ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች በማህበራዊ አጋላጭ ምክንያቶች በአብዛኛው ለድብርት ሊጋለጡ እንደሚችሉም መላ-ምቶች መኖራቸውን ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ጠቅሰዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.