Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ለኮሮና ቫይረስ ቅድመ መከላከል ተግባር ከ256 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ድጋፍ የማሰባሰብ ግብረ ሀይል ለኮሮና ቫይረስ ቅድመ መከላከል ተግባር የሚውል ከ256 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ።

ግብረ ሃይሉ በዛሬው እለት 3ኛ ዙር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አሰባስቧል።

ድጋፉን የክልሉ ባለሀብቶች በገንዘብና በቁሳቁስ ያበረከቱት መሆኑንም ግብረ ሃይሉ አስታውቋል።

በዚህም በዛሬው እለት ብቻ በገንዘብና በቁሳቁስ በድምሩ 11 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ መሰብሰብ መቻሉንም ገልጿል።

በተያያዘም የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሰፋፊ የመገበያያ ስፍራዎች ወደ ሜዳማ ቦታዎች እንዲወጡና ተንቀሳቃሽ ግብይት ስራ ላይ እንዲውል እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ሃላፊ አቶ ዴንጌ ቦሩ ተናግረዋል።

አሰራሩ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚተገበር ሲሆን፥ ነጋዴው እና ሸማቹ በአንድ ስፍራ ሳይገናኝ በትልልቅ ተሽከርካሪዎች አማካኝነት ለሸማቹ የማድረስ ስራ የሚሰራበት ነው ብለዋል።

ሃላፊው ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና ለቫይረሱ መስፋፋት ሚና ያላቸው የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ ጋር ተያይዞም 4 ሺህ የንግድ ተቋማት ሲታሸጉ ለ5 ሺህ ማስጠንቂያ መሰጠቱን እና 157ቱ ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም አስረድተዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.