Fana: At a Speed of Life!

በሃይማኖቶች መካከል የሚኖረው መከባበር ለሰላም መጎልበት እና እድገት መፋጠን የጎላ ሚና እንዳለው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃይማኖቶች መካከል የሚኖረው መከባበር እና ትብብር ለሰላም መጎልበት እና እድገት መፋጠን የጎላ ሚና አለው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

የመጀመሪያው የዓለም ሃይማኖቶች የትብብር ሳምንት ጉባኤ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው ላይ በበይነ መረብ መልእክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ሳኅለ ወርቅ ዘውዴ እንደገለጹት÷በምንኖርበት ዓለም የሃይማኖቶች አዎንታዊ ሚና ሊዘነጋ አይገባም፡፡

የሰዎችን መልካም ሰብዕና ለማጉላት እና ለመገንባት ሃይማኖትን እንደመሳሪያ መጠቀም ይገባል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፥ ጉባኤው በዋናነት አህጉራዊ በሆኑ ጉዳዮች በተለይም በሰላም፣ በሰብዓዊ ክብር፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በዘላቂ ልማት እና በሃይማኖት ነጻነት ላይ የሚያተኩሩ ጭብጦች ላይ እንደሚመክር ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ የመጀመሪያው አህጉር አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት የምክክር ጉባኤ÷ የሃይማኖቶች የላቀ አስተዋጽኦን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በጉባኤው የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ኅብረት ባለስልጣናት፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.