Fana: At a Speed of Life!

የአንጀት ካንሰር መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና ህክምናው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንጀት ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ከትልቁ አንጀት የውስጠኛው ክፍል የሚነሱ ሴሎች ከቁጥጥር ውጭ ሲራቡ የሚፈጠር ነው፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሸምሴ ሸውሞሎ÷ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ፣ሲጋራ ማጤስ ፣የአልኮል መጠጦችን መውሰድ፣የላሙ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ የአንጀት ካንሰር ህመም መንስኤዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በቤተሰብ፣የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ኤፍኤፒ (fap) የተባለ የዘረመል ችግር መኖርና ሌሎች የህመም መንስኤዎች ናቸው ነው ያሉት፡፡

እንደ ዶክተር ሸምሴ ገለፃ÷ የአንጀት ካንሰር ህመም ምልክቶችን ሳያሳይ ሊቆይ የሚችል ሲሆን በዋነኝነት ግን የሰገራ መዛባት፣ሰገራ ላይ ደም መኖር፣የምግብ ፍላጎት ማጣት ፣የአንጀት መነፋትና መፈንዳት ፣ማስማጥ፣ከእንብርት በታች ቁርጠት፣የሆድ ማበጥ፣ተቅማጥ የህመሙ ምልክቶች ናቸው፡፡

ህመሙንም ፎሊክ አሲድ ያላቸውን ምግቦችን እንዲሁም በካልሺዬም እና ማግኒዥዬም የበለፀጉ ምግቦችን በመመገብ፣አትክልትና ፍራፍሬን አዘውትሮ በመብላት ፣የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ ሲጋራ ማጤስና የአልኮል መጠጦችን በማስወገድ መከላከል እንደምንችል የጤና ባለሙያው መክረዋል፡፡

ህክምናዎቹን በተመለከተ ከላይ የተጠቀሱትን የህመሙ ምልክቶች ሲታዩ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ መታየት እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶክተር ሸምሴ÷ ህመሙ የአንጀት ካንሰር ሆኖ ከተገኘም የተለያዩ የህክምና አይነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የህክምና አይነቶቹም የቀዶ ህክምና፣ ኬሞቴራፒ እና ራዲዮቴራፒ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.