Fana: At a Speed of Life!

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከኖርዌይ ልዑክ ጋር በልማት ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከኖርዌይ መንግስት የቴክኒካል ኤክስፐርቶች ቡድን አባላት ጋር በተለያዩ የልማት ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ ስላሉ የልማት ተግባራትና የልማት አጋሮችን ተሳትፎ ስለሚጠይቁ  ጉዳዮች ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ ተደርጓል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ዲጅታል ኢኮኖሚ ቱሪዝም እንዲሁም ሌሎች መስኮችን በመለየትና ትኩረት በመስጠት መንግስት እየሰራ መሆኑ በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አማካሪ ጻድቃን አለማየሁ÷ የልማት አጋሮች ዘርፎቹን እንዲደግፉ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተዋንያን በነዚህ ዘርፎች እንዲሳተፉ መንግስት ፍላጎት አለው ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ አቅም መኖሩን ጠቅሰው÷ ዘንድሮ ስንዴን ኤክስፖርት ማድረግ መጀመሩም የዚሁ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው÷ ለወከላቸው የኖርዌይ መንግስት በኢትዮጵያ ያዩትን ነባራዊ ሁኔታ ካለው የልማት ፍላጎት ጋር በማጣመር እንደሚያስረዱ  ተናግረዋል።

የቡድኑ አባላት የኖርዌይ መንግስት በሃገራት ለሚያደርገው ድጋፍ የሀገራቱን የልማት የድጋፍ ፍላጎት በመዳሰስ የሚያቀርቡ ሲሆን÷ውይይቱም የዚሁ አካል መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.