Fana: At a Speed of Life!

ከ492 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር በማሸሽ በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የሰባት ቀናት ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ492 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር በማሸሽ ሀገሪቷን የውጭ ምንዛሬ አሳጥተዋል ተብለው በተጠረጠሩ ሦሥት ነጋዴዎች ላይ የሰባት ቀናት ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።

አስመጪ ነጋዴዎች ናቸው የተባሉት ተጠርጣሪዎቹ ወይዘሮ ሲትራ መሀመድ፣ ዮናስ አምሳሉ እና ሙክታር መሀመድ ያሲን ይባላሉ።

ተጠርጣሪዎቹ ከጉሙሩክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተወሰኑ ሰራተኞች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከጥቁር ገበያ የተሰበሰበ 492 ሺህ 698 የአሜሪካ ዶላርን ከውጭ ሀገር እንዳስገቡት በማስመሰል እና ሀሰተኛ የጉሙሩክ ዲክላራሲዮን ሰነድ በመጠቀም በጉሙሩክ ሰራተኞች ዲክሌር በማስደረግ ገንዘቡን በማሸሽ ለግል ጥቅም በማዋል በመንግስትና በህዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው መጠርጠራቸውን ተከትሎ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ሲከናወንባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

ይሁንና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ በተጠርጣሪዎች ላይ ላለፉት 11 ቀናት ሲያከናውን የቆየውን የምርመራ ስራ ማጠናቀቁን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስታውቋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በበኩሉ በተጠርጣሪዎች ላይ በፖሊስ የተሰበሰበውን ማስረጃዎች ተመልክቶ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ መሰረት የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበው ለክስ መመስረቻ ተብሎ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ እንደማይገባ የተከራከሩ ሲሆን የዋስትና መብታቸውም እንዲከበር ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ አንቀጽ የሚከሰስ ተጠርጣሪ የዋስትና መብቱ ሊፈቀድለት እንደማይገባ መደንገጉን ገልጾ ተከራክሯል።

ክርክሩን ያዳመጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ ዐቃቤ ህግ ከጠየቀው የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ውስጥ የሰባት ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.