Fana: At a Speed of Life!

እየታየ ያለው የደመና ሽፋንና መጠነኛ ዝናብ ወቅቱን የጠበቀና ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው -ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል እየታየ ያለው የደመና ሽፋንና መጠነኛ ዝናብ ወቅቱን የጠበቀና ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ፡፡

በኢንስቲትዩቱ የሚቲዮሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አሳምነው ተሾመ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ÷ አሁን ላይ የምንገኘው በበልግ ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ሶማሌ፣ ደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች ጉጂ ቦረና እና የተወሰኑ የባሌ አካባቢዎችን ጨምሮ የሲዳማ ክልል የደቡብ ብሄርብሄረሰቦች ክልል እንዲሁም የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ወቅትና እስከ 55 በመቶ የሚሆነው ዓመታዊ የዝናብ መጠን የሚገኝበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች ማለትም የምስራቅ አማራ፣ ደቡብ ትግራይ፣ መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ፣ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች፣ ሐረር እና ድሬዳዋን ጨምሮ ናቸው፡፡

በዚህም በተለይ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የዝናብ ሁኔታ ይኖራቸዋል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም የሰሜን አጋማሽ አብዛኛው አማራ፣አፋር መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ካለፈው አርብ ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በስምጥ ሸለቆ የሀገሪቱ አካባቢዎች ምስራቅ አማራ፣ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የተስፋፋ እና የተጠናከረ የደመና ክምችት እንደነበራቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በብዙ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከፍተኛ ዝናብ መመዝገቡንም ነው የሚቲዮሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሪ ስራ አስፈፃሚው የተናገሩት፡፡

በዚህም እየታየ ያለው የደመና ሽፋንና ዝናብ ወቅቱን የጠበቀና በሚቀጥሉት አስር ቀናትም በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

በዚህም ከቀላል እስከ ከባድ ዝናብ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ፣ኢሉባቡር ፣ ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን እንዲሁም ሐረር እና ድሬዳዋ፣ በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ ሰሜ ሸዋ ዞን፣ በትግራይ ክልል የደቡብ ትግራይ አካባቢዎች፣ አብዛኛው የአፋር ክልል የደቡብ፣ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልልና የሲዳማ ክልል አብዛኛው አካባቢዎቻቸው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ ያገኛሉ ነው ያሉት፡፡

በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ደግሞ ማለትም በሰሜን ምዕራብ ፣በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ምስራቅ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከ35 ዲግሪ ሴሊሽየስ በላይ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የበልግ አብቃይ አካባቢዎች የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ እየተመዘገበ ነው፤ ይህም መሬትን ለእርሻ ከማዘጋጀት እንዲሁም ከመኖ እና ከውሃ አቅርቦት ጋር ተያይዞ አዎንታዊ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.