Fana: At a Speed of Life!

የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 273 ተማሪዎች በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሙሉ ስኮላርሺፕ መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 273 ተማሪዎች የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ሙሉ ስኮላርሺፕ መስጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

በዛሬው ዕለት የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ወስደው ከግማሽ በላይ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች ውስጥ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 273 ተማሪዎች እውቅና ተሰጥቷል፡፡

የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና በተሰጠበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸው፥ “ለተማሪዎቹ እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላ የተሰጣቸውን ፈተና በአግባቡ መስራት በመቻላቸው ኢትዮጵያን የሚያግዙ 273 ተማሪዎች ተገኝተዋል በዚህም ደስታ ይሰማናል” ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉና ለኢትዮጵያ እና አፍሪካ የሚደርሱ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ተማሪዎቹ በርትተው ተምረው ሀገራቸውን ሳይረሱ የሚጠቅሙ እንዲሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

“ሁሉም ተማሪ ጥበብን እንዲሻ እና ሀገሩን ለመለወጥ እንዲሰራ ጠይቀዋል፤ በተለይም ለእውነት የቆመ ተማሪ ነገ ሃገሩን ይለውጣል፤ እናንተ የላቀ ውጤት ያስመዘገባችሁ ተማሪዎችም እውነትን የምትሹ መሆን አለባችሁ እንደዛ ሲሆን ደግሞ ሀገርን የምትገነቡ ትሆናላችሁ ብለዋል።

“በትውልዶች ግንባታ ላይ ነው፤ ያለፈው ትውልድ አልፏል አሁን ያለው ትውልድም አነሰም በዛም ለሀገሩ እየለፋ ነው፤ እናንተ ግን ገና ከምንጩ ለሀገራችሁ የምትጠቅሙ እንድትሆኑ ከሰፈራችሁ ወጣ ብላችሁ ለሀገር እንድታስቡና ቀድሞ የነበሩ ስመጥር ኢትዮጵያውያን ምሁራን ከእናንተ ውስጥም እንዲወጡ አደራ እንላችኋለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፥ “እንደ መንግስትና ትምህርት ሚኒስቴር የተጀመረው ለውጥ የፈተናዎችን ቅቡልነት በማረጋገጥ ቢሆንም በሁሉም መስኮች የሚስተዋሉ የትምህርት ስብራቶችን መጠገንና በሁሉም መመዘኛ ብቁ የሆኑ ተማሪዎችንና ጠንካራ ዜጎችን ለመፍጠር እንተጋለን” ብለዋል፡፡

በዚህ የለውጥ ሂደት ደግሞ ተጠቃሚውም ተጎጂውም ህብረተሰቡ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ በቀጣይም ብቁ ተማሪዎችን የመፍጠሩ ሂደትና የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

እውቅና የተሰጣቸው ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት መስክ ከ700 ድምር ውጤት ከ600 በላይ ያመጡ 263 ተማሪዎች እና በማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ከ600 ድምር ውጤት ከ500 በላይ ያመጡ 10 ተማሪዎች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በአላዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.