Fana: At a Speed of Life!

በገንዘብ ሚኒስትሩ የተመራ ልዑክ ከቻይና የፋይናንስ ተቋማት ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑካን ቡድን ከቻይና ዋና ዋና የፋይናንስ ተቋማት ጋር የኢንቨስትመንት ትብብርን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል፡፡

ልዑካን ቡድኑ ከቻይና ኤክስፖርት እና ኢምፖርት ባንክ፣ ከኢንዱስትሪ እና ንግድ ባንክ፣ ከልማት ባንክ፣ከኤክስፖርት እና ብድር ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን እና ከዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ የስራ ኃላፊዎች ጋር የነበረው ውይይት ውጤታማ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በውይይታቸውም÷በቀጣይ ከሚኖሩ አዳዲስ እና ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ዋንኛ የትኩረት መስኮች ጋር በተያያዘ ሀሳብ መለዋወጣቸው ተመልክቷል።

ልዑካን ቡድኑ ለፋይናንስ ተቋማቱ በኢትዮጵያ በኩል የግሉ ዘርፍ በቴሌኮም፣የፋይናንስ ዘርፍ፣ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ኢነርጂ እና ግብርና ዘርፍ ለማሳተፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ላይም ገለጻ መደረጉ ተመላክቷል፡፡

ሁለቱ ወገኖች አዳዲስ ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት መስኮችን በማፈላለግ ባለፉት 10 ዓመታት የገነቡትን ስኬታማ የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.