Fana: At a Speed of Life!

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና የብሉ ናይል ግዛት የሠላምና የልማት ኮንፈረንስ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በሱዳን የብሉ ናይል ግዛት የሠላም እና የልማት ኮንፈረንስ በብሉ ናይል ግዛት ዋና ደማንን ከተማ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
 
በኮንፈረንሱ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ የብሉ ናይል ግዛት ፕሬዚዳንት ጀነራል መሐመድ አልዑምዳን ጨምሮ የሁለቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
 
“ሠላም፣ ልማት እና መልካም ጉርብትና” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ኮንፈረንስ ባለፉት ጊዜያት በጋራ የተከናወኑ የሠላም፣ የጸጥታ እና የልማት ሥራዎች አፈጻጸም ቀርቦ የሚገመገም ይሆናል።
 
በቀጣይም የህዝቦችን አብሮነት የሚያጠናክሩ፣ በሠላም እና በልማት የሚሠሩ ሥራዎችን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስችሉ የጋራ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል፡፡
 
መድረኩ በተለይም የመረጃ ልውውጡን የበለጠ በማሣደግ በድንበር አካባቢ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በአፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑም ተጠቅሷል።
 
መልካም ጉርብትናን ከማጠናከር ባለፈ፣ ሁለቱን ህዝቦች በሕዝብ ለሕዝብ እና በንግድ ለማስተሣሠር እየተከናወኑ የሚገኙ ተጠናክረው የሚቀጥሉባቸው አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጡም ይጠበቃል።
 
 
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና የብሉ ናይል ግዛት ህዝቦች አብሮነት፣ ሠላምና ልማት ለማረጋገጥ በጋራ ባከወኗቸው ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገቡንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.