Fana: At a Speed of Life!

በቦረና ዞን በድርቁ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገ ነው – አቶ አወሉ አብዲ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦረና ዞን በድርቁ ለተጎዱት ዜጎች ድጋፍ እየተደረገ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አወሉ አብዲ ተናገሩ፡፡

እንደ ዓለም የተከሰተው የአየር ሁኔታ መዛባት በኦሮሚያ ክልል 10 ዞኖች ላይ የውሃ እጥረት አስከትሏል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ በእነዚህ ዞኖች እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነም ገልፀዋል።

እስካሁን ለ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነም ነው የተናገሩት።

በዛሬው ዕለት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እንዲሁም የአየር ሀይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በቦረና ዞን ተገኝተው ጉብኝት እያደረጉ ነው።

በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አወሉ አብዲ ፥ በዞኑ ያጋጠመውን የድርቅ ችግር ለማለፍ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአጭር ጊዜ እቅድም አፋጣኝ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እየተደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ከረጅም ጊዜ እቅድ አኳያ ክልሉ ወደ 5 ቢሊየን ብር መድቦ 18 ትንንሽ የውሃ ግድቦች እየተሰሩ አንደሆነና ከእነዚህ ውስጥም አንዱ ተጠናቆ ሲመረቅ ሌሎች 12 ወደ መጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ከዚያ ባለፈም የውሃ ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ እየተደረገ ነው ያሉ ሲሆን ፥ በቀጣይም ዘላቂነት ያለው ስራ እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት።

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.