Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫ፣ የአሸናፊነትና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ነው- ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫ፣ የአሸናፊነትና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡

የአማራ ክልል ለ127ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ በመልዕክታቸው÷ ድሉ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ክብርና ኩራት ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ጭምር ነው ብለዋል።

ዓድዋ የነጻነትና የሀገር ሉአላዊነት መሐንዲስና አርበኛ በሆኑት አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በሰጡት ወታደራዊ የአመራር ጥበብ መላ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት በመሆኑ ኢትዮጵያ በነጻነቷ ጸንታ እንድትዘልቅ አስችሏታልም ነው ያሉት።

ዓድዋ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አዲስ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ታሪክ የተመዘገበበት እንጂ ወታደራዊ ድል ብቻ አይደለም ሲሉም ነው የገለፁት።

ጀግኖች አባቶቻችን የጠላት ኃይል ሚዛን ሳይበግራቸው ጦርና ጎራዴ አንግበው በተባበረ ብርቱ ክንድና መስዋዕትነት ጠላትን አንበርክከው ጀግንነትና አርበኝነትን፣ ክብርና ነጻነትን አውርሰዋለ፤ የሀገራቸውን ሉአላዊነት በጽኑ መሠረት ላይ አኑረዋል፤ አንጸዋል፤ ለሀገራቸው ክብርን አጎናጽፈዋል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

በአንድነት፣ በፍትህና በእውነት የጸና ሕዝብ ሁልጊዜም አሸናፊና ባለድል እንደሚሆን አያጠራጥርም፤ የአሸናፊነትና ድል አድራጊነታቸው ምክንያት ደግሞ ሀገራዊ ፍቅርና የስነልቦና አንድነት ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው።

ነጻነትና ክብር ያለ መስዕዋትነት፣ ድልና ጀግንነት ያለ ተጋድሎ መጎናጸፍ አይታሰቡም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የአርበኝነት አርማ፣ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ አሻራና ሰብአዊ ክብር የተረጋገጠበት ታላቅ ድል እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡

እብሪተኝነትና ግፈኝነት ከሽፎ እውነትና ፍትሕ አሸናፊ የሆኑበት ክስተትን ከዓድዋ ድል የምንማረው ነውም ብለዋል።

ስለሆነም የዓድዋ ድል 127ኛ ዓመት ስንዘክር ልዩነቶቻችንን ሁሉ ወደ ጎን ትተን ህብረትን፣ መተባበርንና ሀገራዊ አንድነትን መርህ ማድረግ ይኖርብናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ127ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.