Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለ127ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

 አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ 127ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን በመስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ዓድዋ የድል ሜዳ ብቻ ሳይሆን በአንድነት የመቆም የድል ሚስጥር ነው ብለዋል፡፡
 
አፍሪካን ለመቀራመት፣ ሃብቷን ለመዝረፍና የራሱን ማንነት ለመጫን የመጣውን እብሪተኛ ኢትዮጵያውያን በዝምታ እንዳልተቀበሉትም አንስተዋል፡፡
 
ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቀው የመጡትን ቅኝ ገዢዎች በመመከት በብዙ የጦር አውድማዎች በጀግንነት ተዋግተው ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸውንም ነው የገለጹት።
 
የዓድዋ ጦርነት ድል የሚገኘው በቁርጠኝነትና በአንድነት ብቻ መሆኑን ያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
 
በዓድዋ ድል ጥቁር ነጭን ማሸነፍ እንደሚችል አሳይቷል ፤ እናም ለአፍሪካውያን የነፃነት ምልክት እና ለቅኝ ገዥዎችም ውርደት ሆኗል ሲሉም ነው ያነሱት ።
 
ኢትዮጵያውያን በጋራ በዓድዋ ተራራ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ጠላትን በማሳፈር የማይረሳ የጀግንነት ታሪክ ማስመዝገባቸውን አስታውሰዋል፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም በዓድዋ የታየው ጀግንነት እና የሀገር ፍቅር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የሚደርስባትን በነጻነቷ ላይ የሚደርስ ጥቃት እንድትቋቋምና ክብሯን እንድትጠብቅ አስችሏታል።
 
በአባቶቻችን ደምና አጥንት የተከለለች ሀገር ፈተናዎቿን በማሸነፍና ወደ መልካም እድል በመቀየር ጠንክራ እንድትቆም አንድነትና አብሮነት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.