Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል  የዓለምን የጥቁር ህዝቦች ታሪክ የቀየረ አስደማሚ ሁነት ነው -አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል በጨለማው የጥቁሮች ሰማይ ስር የነጻነትን ብርሐን የከሰተ አብሪ ኮከብ እንዲሁም የዓለምን የጥቁር ህዝቦች ታሪክ የቀየረ አስደማሚ ሁነት ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለ127ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም የዓድዋ ድል ብዝኀ ማንነቶች ለአንድ ዓላማ ተሰልፈው የማይሰበር የሚመስለውን የአውሮፓን የቅኝ ግዛት ቀንበር እንዳይፈራርስ ሆኖ ለዘመናት የተገነባውን የሮማን ኢምፓየር በሚያስደንቅ ጀብዱ ያንኮታኮቱበት አስደናቂ የታሪክ ክስተት ነው ብለዋል።

የዛን ጊዜው ትውልድ አንጸባራቂውን ድል የተቀናጁት በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታግዘውና በወታደራዊ ሳይንስ ተክነው ሳይሆን አንድነታቸው ጉልበት፣ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ስንቅ፣ የአያት ቅድመ አያቶቻቸው የጀግንነት ታሪክ ወኔና ጥበብ ሆኗቸው ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በዚህ የጦር ግንባር ውሎ አንድነት ከዘመናዊ የጦር መሣሪያ በልጦ መታየቱን ጠቅሰው÷የሀገር ፍቅር ስሜት ከወታደራዊ ሳይንስ ልቆ ተገኝቷልም ነው ያሉት፡፡

ጥቁርነት ጽናት፣ ኢትዮጵያነት ደግሞ ኩራት መሆኑን ዓለም ምስክርነቱን እንዲሰጥ ሆኗል ያሉት አፈጉባዔው÷ የእንግሊዝ ጋዜጦች በፊት ገጻቸው የዓለም ታሪክ ተገለበጠ፤ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪቃ ተቀሰቀሰ ብለው እንዲጽፉም ተገደዋል ብለዋል፡፡

የዓድዋን ድል ስናከብርም ሆነ ስናስታውስ ንጉሥ ምኒልክንና እቴጌ ጣይቱን እንዲሁም ጀግኖች የጦር አበጋዞቻቸውን መዘከር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት፣ ሀገራዊ አንድነትን በማጽናት የግዛት አንድነቷ የተከበረ፣ ልማቷ የተፋጠነ፣ ሰላሟ የተጠበቀና ለሁሉም ዜጎች የምትመች ኢትዮጵያን በመገንባት የራሱን አኩሪ ታሪክ ሠርቶ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የጋራ ድምር ውጤት መሆኑን በመጥቀስም በአጥንታቸው ክስካሽ ኢትዮጵያዊነትን በጽኑ መሠረት ላይ አቁመዋል ነው ያሉት፡፡

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን የፅናት አብነት፣ የኩራት ምንጭ ነው፤ የ“የይቻላል” ወኔን የሰነቅንበትና በዓለም አደባባይ ቀና ብለን እንድንታይ ያስቻለንም ነው̎  ሲሉም ነው የገለጹት።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ያበረከተችው ስጦታና ለነጻነት ትግሉ ፋናወጊ ሆኖ የመራ መሆኑን ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ስንቆም ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ወንድሞቻችን ፋናወጊ እንሆናለን፤ ለዓለምም የምናበረክተው መልካም ስጦታም ይኖረናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የዓድዋን የድል በዓል ስናከብር በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል ማለታቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

#Ethiopia #Adwa #Victory

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.