Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ አጠናክራ ትቀጥላለች – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ጉባዔ ለመሳተፍ አዘርባጃን ርዕሰ መዲና ባኩ ትናንት ገብተዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ከአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄይሁን ባይራሞቭ ጋር በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል ።

አቶ ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት ፥ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረክ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል።

እያደገ የመጣውን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር በቀጣይነት እንሰራለንም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በመከላከያ እና ፀጥታ፣ በአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ እና በፐብሊክ ሴክተር ከአዘርባጃን ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላትም ጠቅሰዋል።

የአዘርባጃን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ፥ በቀጣይነት ሀገራቱ የፖለቲካ ምክክር ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውም አንስተዋል።

የአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄይሁን በበኩላቸው ፥ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።

አያይዘውም በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት የወሰደውን ኃላፊነት እና ቁርጠኛ አመራር አድንቀዋል።

አዘርባጃን በትምህርት ትብብር የኢትዮጵያ ተማሪዎች በሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲማሩ ነፃ የትምህርት ዕድል እንደምትሰጥም ነው የገለጹት።

የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ጉባዔ ከነገ ጀምሮ በአዘርባጃን ርዕሰ መዲና ባኩ ይካሄዳል ።

በጉባዔው ኢትዮጵያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተመራ ልዑክ እንደምትሳተፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.