Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ኩራት እና የአንድነት ኃይል ነው – የጦር ታሪክ ተመራማሪ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ኩራት እና የአንድነት ኃይል ነው ሲሉ የወታደራዊ ታሪክ ተመራማሪ እና ደራሲ ጥላሁን ጣሰው ገለጹ፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል፣ የወታደራዊ ታሪክ ተመራማሪና ደራሲ ጥላሁን ጣሰው ÷ የዓድዋ ድል የታሪክን ተለምዷዊ ሂደትን ባልተለመደ መልኩ የቀየረ ድል ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የዓድዋ ድልን በተመለከተ ከወታደራዊ ታሪክ ተመራማሪና ደራሲ ጥላሁን ጣሰው ጋር ቆይታ ነበረው፡፡
እንደ ታሪክ ተመራማሪው የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ የጋራ ማንነት እንዲያጎለብቱ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
ድሉ የኢትዮጵያን ወታደራዊ ኃይል ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደነበረውም ጠቁመዋል፡፡
በወቅቱ የተገኘው ድል ለኢትዮጵያውያን ብርታት ሆኖ በመጀመሪያ ጣሊያን ፣ ቀጥሎም እንግሊዝ የፈፀሙትን ወረራ በመልሶ ማጥቃት መቀልበስ እንዳስቻለም ያስረዳሉ፡፡
ጣሊያን በቁጭት ተመልሶ ለወረራ ቢመጣም የዓድዋ ድል ወኔ ባለመብረዱ ጣሊያንን እና እንግሊዝን እንደየአመጣጣቸው መመለስ እንዳስቻለም አውስተዋል፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን የውጭ ጠላት ሲወራቸው አንድ ሆነው እንዲቆሙ እና የጋራ ግብ አንግበው ባልሸነፍ ባይነት ወኔ እንዲዋጉ ያስቻለ የጋራ ማኅተም ነውም ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል ታሪክ ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው የጥቁር ህዝቦች ኩራት እና የአንድነት ኃይል መሆኑንም ያስረዳሉ።
የታሪክ ተመራማሪው “ዓድዋ” እና “ፓን አፍሪካኒዝም” የማይነጣጠሉና “አፍሪካ ለአፍሪካውያን” ከሚለው ዕሳቤ የመነጩ መሆናቸውንም ነው የሚገልጹት፡፡
ከዓድዋ ድል በፊት አፍሪካውያን አውሮፓውያንን በጦርነት መቋቋም ያልቻሉት እና የተሸነፉት ጠንካራ ወታደራዊ ኃይልና መሣሪያ ስላልነበራቸው መሆኑን ታሪክ ጠቅሰው አስታውሰዋል፡፡
በወቅቱ አፄ ምኒሊክ ከአውሮፓ ጋር የሚገዳደር ዘመናዊ ወታደራዊ ኃይል በመገንባታቸው ጦርነቱን ማሸነፍ እንደቻሉም ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ ድል በርካታ ትምህርቶችን መውሰድ እንደሚችሉ የሚገልጹት የታሪክ ተመራማሪው፥ ከድሉ በኋላ የተከናወኑ ተግባራት የህዝቡን አንድነት ማስጠበቅ የቻለ መሆኑንም አውስተዋል።
በዮናታን ዮሴፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.