Fana: At a Speed of Life!

ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነዉ – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2025፣ (ኤፍ ቢ ሲ) ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነዉ ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

አገልግሎቱ 127ኛው የዓድዋ ድል በዓልን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነዉ!

የካቲት 23/1888 ዓ.ም አባቶቻችን የተጎናፀፉት የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ነፃነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ሊገፍ የመጣውን የሰለጠነ ወራሪ ጦር በታላቅ በጀግንነት ወኔ፣ በአንድነትና በጽናት ያሸነፉበት እለት ነው፡፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በአንድ የፍቅር ገመድ ያሰናሰለ የነፃነት እና ሉዓላዊነት ብስራት ነዉ፡፡

ድሉ የኢትዮጵያ ሕብረብሔራዊ አንድነት የጸናበት የማዕዘን ድንጋይም ነው፡፡

የዓድዋ ድል ከጊዜያዊ ውጤቱ ባሻገር የዓለም የሰው ልጆችን ታሪክ ጭምር የቀየረ በደማቅ ቀለም የተፃፈ ድል ነው፡፡

ድሉ ከማሸነፍም ባሻገር የኢትዮጵያዊ አንድነት የፀናበትና የመተባበራችን ዉጤት ማሳያ መስታወት ሆኖ ሲዘከር ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ልጆች ለአንድ የጋራ ሀገራቸው ከአራቱም አቅጣጫ በአንድ ጥሪ ተሰባስበው፤ የጋራ ጠላትን ድል በመንሳት ሕልውናቸውን ያረጋገጡት አንዱ እና ዋነኛዉ በዓድዋ ድል ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥቅማቸው የሚከበረው በመተባበር እንጂ በመለያየት እንዳልሆነም የዓድዋ ድል ኽያዉ ምስክር ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ለአንድ ዓላማ፤ በአንድነት አብረው በጋራ ሲሰለፉ ምን አይነት ውጤት እንደሚያመጡ በዓድዋ ድል ተረጋግጧል፡፡

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ነፃነትን ያበሰረ ነበር፡፡

የአድዋ ድል ለፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ መፀነስ ትልቅ መሠረት የጣለ ክስተትም ሆኗል፡፡

በዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የነበራቸው የአመራር ብቃት፣ ፅናት፣ ጀግንነትና የዓላማ አንድነት ምንግዜም የሚታወስ ነዉ፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን በውስጣቸው የነበረዉን ልዩነት ወደ ጎን በመተዉ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ለማፅናት በጋራ መቆማቸዉ የዓድዋን ድል እንድንጎናፀፍ አድርጎናል፡፡

የዓድዋ ድል መንፈስ በቀጣይ ተከታታይ ትውልዶች አዕምሮ ውስጥ የተቀረፀ የድል ሐውልት በመኾኑ፤ ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ሀገራዊ ፈተናዎች በጋራ ርብርብ መፍታት እደምትችል ቁምነገር ያስጨበጠ ነው፡፡

የዛሬው ትውልድ በአድዋ ድል የታየውን የአባቶቹን ጀግንነት፤ አንድነት እና የዓላማ ፅናት በተለያዩ መስኮች መድገም ይኖርበታል፡፡

በዘመናችንም በሕዳሴው ግድብ ግንባታ፤ የአሸባሪዎችን ጥቃት በመመከት፤ በአረንጓዴ አሻራ፤ እና በሌሎችም መስኮች የታየው ሕብረትና ያመጣው ውጤት፤ በዓድዋ ድል መንፈስ መንቀሳቀስ ውጤቱ አጥጋቢ እንደሚኾን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

የዛሬዉ ትዉልድ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆም የሀገራችንን የብልፅግና ጉዞ ከግቡ ማድረስ እንደምንችል ከዓድዋ ድል ትምህርት መዉሰድና በተሰማራንበት መስክ ሁሉ የአባቶቻችንን የአሸናፊነት መንፈስ በመሰነቅ ለአገራችን የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ127ኛዉ የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!!

ዓድዋ፡ አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት!!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.