Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል ለፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዋና መሰረት ነው – ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል ለፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዋና መሰረት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ባለው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የዓድዋ ድል ብዙ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል፡፡

በወቅቱ በነበሩት መሪ አጼ ሚኒሊክ የተመራው ጦርና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የጦር መሪዎች፣ አርበኞች፣ የክተት ጥሪ የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ሊወር የመጣን ጠላት በማሸነፍ ኢትዮጵያን የቅኝ ተገዢ ከመሆን አድነዋታል ብለዋል፡፡

በዚህም የዓድዋ ድል በአፍሪካ የቀኝ ግዛት መስፋፋት በያዘው ፍጥነት እንዳይቀጥል በከፍተኛ ደረጃ የገታ ነውም ብለዋል፡፡

ድሉ ለዘመናዊቷ አፍሪካ ምስረታ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረገ መሆኑን አንስተውም ፥ ለፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዋና መሰረት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተወረረችበት ጊዜም በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያሉ ጥቁሮች የነጻነት ቀንዲላቸው እንዳትነካ ለመዝመት የተነሱበት እንደነበርም ነው ፕሬዚዳንቷ ያስታወሱት።

በዚህም ‘’አንድ የነጻነት ተምሳሌት ብትኖረን፣ አንድ ነጻ ጥቁር መንግስት ያውም የነጭ ሰራዊትን ያሸነፈ ቢኖረን ለሁላችን አርዓያና ተምሳሌት አለን በምንልበት ዘመን እንዴት እርሷን ኢትዮጵያን ለመውረር ይታሰባል’’ በማለት መነሳታቸውንም አውስተዋል፡፡

ይህን ድል ያስመዘገቡልንን አጼ ሚኒሊክና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ፣ የጦር መሪዎች፣ አርበኞች ብቻ ሣይሆኑ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በባህልና በሃሳብ የሚለያዩ ኢትዮጵያውያን ጭምር እንደሆኑም አንስተዋል፡፡

በዚህም ምንም ያህል በሃሳብና በአቋም ብንለያይ አንድ የሚያደርገን ሀገር ስላለን በመነጋገርና ልዩነትን በማጥበብ ተከባብሮ መኖር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ አክለውም ፥ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊም አፍሪካዊም ብቻ አይደለም፤ ለነጻነት፣ ለሉዓላዊነት፣ ከጭቆና ለመላቀቅ ለሚታገሉ ሁሉ የአንድነት፣ የመተባበር የማሸነፍ ተምሳሌት እንደሆነም ነው ፕሬዚዳንቷ የገለጹት፡፡

አብሮ ለማደግ መፍትሄ መፈለግ፣ ስክነት፣ ቻይነት፣ መወያየት፣ መከባበር እንዲሁም አንድነት ለሀገር ግንባታ ጥረት አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ዓድዋ የሴቶች ሚና ጎልቶ የታየበት በመሆኑ ሌላው አኩሪ ገጽታ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

አንድ ሀገራችንን አብረን እንገነባለን ካልን ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል ያሉት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ፥ ብሔራዊ ስሜትን በየጊዜው ማዳበር ለአንድነታችን ጠንካራ መሰረት ነው ሲሉ አንስተዋል፡፡

ቀደምት አባቶቻችን በታላቅ ተጋድሎ ያስረከቡንን ሀገር ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ፈንታ ብቻ ሣይሆን ግዴታውም ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን አሳልፋለች ፤ እያሳለፈችም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፥ ለተፈናቀሉ ወገኖች፣ በድርቅና በጦርነት ለተጎዱት ተባብረን የጋራ መፍትሄ ማግኘት የመላው ኢትዮጵያውያን ሥራ ነውም ብለዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.