Fana: At a Speed of Life!

አሮጌ ጫማ ለማደስ በተከራዩት ቤት ውስጥ 1 መትረየስና 7 ክላሽ ጠመንጃ ሸሽገው የተገኙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አሮጌ ጫማ ለማደስ በተከራዩት ቤት ውስጥ መትረየስና ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ደብቀው የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ፖሊስ መምሪያው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ሳጥን ተራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በአንድ የአሮጌ ጫማ ማደሻ ቤት ላይ ባደረገው ፍተሻ ሰባት ክላሽንኮቭ እና አንድ መትረየስ ጠመንጃ ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር ይዞ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ኃላፊ ኮማንደር ጌታነህ በቀለ ገልፀዋል።

ፖሊስ የመሳሪያውን ምንጭ እና ለምን ተግባር ሊውል እንደነበር ለማወቅ ምርመራውን መቀጠሉን ኃላፊው አስረድተው ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው በማረፊያ ቤት ይገኛሉ ብለዋል።

አዲስ በፀደቀው የጦር መሳሪያ አዋጅ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ማዘዋወርም ሆነ ይዞ መገኘት የሚያስከትለው ቅጣት ከፍተኛ መሆኑ ወንጀሉን ለመከላከል የራሱ ጠቀሜታ ይኖረዋል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.