Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰጠው መግለጫ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዚያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ በሀገራችን ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደኅንነት ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመመከት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዝር ሲመክር ቆይቶ የተለየዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያውያን

ውድ የሀገራችን ሕዝቦች

ፓርቲያችን ሀገራዊ ለውጡን በመምራት ሂደት እያጋጠሙ የነበሩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ችግሮችን ለመቅረፍ የተቀናጀና መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ተጨባጭ ውጤቶችን አምጥቷል።

ለውጡ ኢትዮጵያን ፍትሕ የሰፈነባት፣ በዴሞክራሲ የዳበረች፣ በሰብአዊ መብት ጥበቃ የተመሰገነች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ በሰላምና በደህንነት የተረጋጋች ሀገር ማድረግ መሆኑን በማመን ከዴሞክራሲ ሪፎርሙ ጎን ለጎን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ተግባራት ለፍሬ በቅተው ከሞላ ጎደል ወደ ሰላማችን ተመልሰናል።

ለሰብዓዊ መብትና ለጋራ ተጠቃሚነት ዕንቅፋት የሆኑ ሕጎችና አሠራሮች ተስተካክለዋል። በሁሉም አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከሞላ ጎደል ሁሉም ወደ ቀያቸው ተመልሰው የዕለት ተዕለት ኑሮ ጀምረዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡን እያማረሩ የነበሩ ታጣቂዎች እና የጎበዝ አለቆችን አደብ ለማስገዛት በተወሰደ እርምጃ ሥርዓት አልበኝነትን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ተችሏል።

ኢኮኖሚያችን ከቀውስ ወጥቶ ማንሠራራት ጀምሯል። ሀገራችን ለበርካታ ጊዜ ያካበተችውን መልካም የዲፕሎማሲ ወረት በመጠቀም ከጎረቤት ሀገራት እና ከተቀረው የዓለማችን ክፍል ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ተጠናክሯል። በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መካከል፣ በሱዳን የሽግግር ሂደት እና በኬንያ እና ሶማሊያ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተሠሩ ተግባራት የዲፕሎማሲ ተሰሚነታችንን ያሳደጉ ሆነዋል።

ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድን በመከተል በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለመጋፋት የሚደረገውን ጥረት ለማክሸፍ በፅናት ታግለናል። በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻችንን መብትና ጥቅም ለማስከበር ተችሏል።

ክቡራትና ክቡራን

በጥቅሉ ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እያመራ የነበረውን ሀገራዊ ሁኔታችንን በማስተካከል፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ ሀገራችን ብልፅግና እና ስለ ወደፊቷ ጠንካራ ኢትዮጵያ ማሰብና መስራት በጀመርንበት በዚህ አጓጊ ወቅት በዓለማችን በፍጥነት በመዛመት ሁለንተናዊ ቀውስ እያስከተለ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገራችንም ተከስቷል።

ቫይረሱ እስካሁን 200 በሚጠጉ ሀገራት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሏል፤ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ወደ 100 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ደግሞ የሞት ምክንያት የሆነው ይህ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ገብቶ 65 ዜጎቻችን ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል።

ከእነዚህ ውስጥ ለ3 ዜጎቻችን ኅልፈት ሕይወት ምክንያትም ሆኗል። ነገ ምን ያህል ዜጎቻችንን እንደሚያጠቃ በእርግጠኝነት ባናውቅም ሁላችንም ተረባርበን አስከፊ ጉዳት እንዳያደርስብን መዘጋጀትና ችግሩን ለመሻገር ተስፋችንን ለማስቀጠል መረባረብ ይጠበቅብናል።

የተደቀነብንን ፈተና ለማለፍ፣ በሽታውን ለመከላከል፣ ለማከምና ተዛማጅ ጉዳቶቹን ለመቀነስ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግሥት በትኩረት መንቀሳቀስ አለብን። በዚህ ወቅት ለብልፅግና ፓርቲ ሕዝባችንን ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ ከመከላከልና ከማዳን የሚበልጥ ተልዕኮ የለም።

ፓርቲያችን ከጅምሩ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ለዚሁ ስራ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፥ ብሔራዊ የወረርሽኝ መከላከል ኮሚቴና ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም ከላይ እስከታች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ሀገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮቹን ቀዳሚ ተልዕኳቸው ወረርሽኙን መከላከል ስራ አድርጎ አሰማርቷል። ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የተወሰዱት እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን የገመገመው ፓርቲያችን የቀጣይ ጊዜያት ዋና ተልዕኮና ተግባራችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከል መሆኑን በማመን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።

1ኛ. ከፊት ለፊታችን የተደቀነውን ፈተና በአሸናፊነት ለመወጣትና ሕዝባችንን ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ መከላከል፣ ማከምና የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጣር መቻል፤ እንዲሁም ተዛማጅ ጉዳቶቹን ትርጉም ባለዉ መልኩ ለመቀነስ፤ በዚህ ወቅት ፓርቲያችን ከዚህ የሚበልጥ ተልዕኮ አለመኖሩን በመገንዘብ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ እንዳለብን ከመግባባት ተደርሷል።

2ኛ. የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ነጻ እና ምቹ ሀገራዊ ሁኔታን ይፈልጋል። በመሆኑም ቫይረሱን ለመቆጣጠር የምንሠራቸው ሥራዎች ከዘላቂ የዴሞክራሲ ግንባታ ግባችንን የማይጣረሱ እንዲሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በየደረጃው የሚወሰዱ እርምጃዎች ሕግና ሥርዓትን የተከተሉ፣ የጀመርነውን የዴሞክራሲ ጉዞ የማያሰናክሉ፣ ነገር ግን ደግሞ ወረርሽኙ የሚፈልገውን የአስቸኳይ ጊዜ ባሕሪያት የተረዱ መሆን እንዳለባቸው መግባባት ላይ ደርሰናል።

3ኛ. ወረርሽኙን በድንገት እንደታወጀብን ጦርነት በመሆኑ በፍጥነት ጥቃት እያደረሰብን ያለና እንደማንኛውም ጦርነት በኢኮኖሚያችን ላይ የራሱን ከባድ ጫና ሊፈጥርብን ይችላል። ይህን ቫይረስ ለመቆጣጠር የምናደርገው ዘመቻም ሀብታችንንና የሰው ኃይላችንን ስለሚሻማ በኢኮኖሚያችን ላይ ሊፈጥረው የሚችለው ጫና ከፍተኛ እንደሚሆን እንረዳለን። በመሆኑም የወረርሽኝ ቁጥጥር ሥራችን ኢኮኖሚያችንን በእጅጉ እንዳያናጋና ቀጣይ የብልፅግና ትልማችንን እንዳያደናቅፍ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና ገበያውን ለማረጋጋት በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንዳለብን ስምምነት ላይ ደርሰናል።

4ኛ. የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በሚደረጉ ርብርቦች መካከል የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ እንዳይስተጓጎል፣ የኑሮ ውድነት እንዳይጨምርና የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎቶች በተቻለ መጠን እንዳይጓደሉ ለማድረግ ከፍተኛ ዝግጁነት ያስፈልጋል።

ወረርሽኙ በዜጎች ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን ማኅበራዊ ጉዳት በመንግሥት አቅም ብቻ ለመፍታት አይቻልም። ስለሆነም ከመንግሥት በተጨማሪ ሕዝባችን በዳበረ የእርስ በእርስ የመረዳዳት ባህሉ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን እንዲታደግ፤ ማስተባበርና ይህን ሀገራዊ ፈተና እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ሕገ ወጦችን ከድርጊታቸው ለመግታት ከምንጊዜውም የተለየ የሕግ ቁጥጥር አስፈላጊ እንደሆነ መግባባት ላይ ተደርሷል።

5ኛ. በዚህ የወረርሽኝ ወቅት ብሔራዊ ደኅንነታችን እና ሉአላዊነታችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ በማድረግ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፉ በማናቸውም መንገድ ለመከላከልና አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ ሁሉ ለመውሰድ ዝግጁ መሆን እንዳለብን መግባባት ላይ ተደርሷል።

የተከበራችሁ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች

ፓርቲያችን ለየትኛውም ፈተና የማይበገር፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በፅናት ታግሎ ማለፍ የሚችል ፓርቲ ለመሆኑ እናንተ ህያዋን ምስክሮች ናችሁ። ዛሬም በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ተጋረጠውን ይህን ክፉ ወረርሽኝ መላው ህዝባችንን በማስተባበር በድል አድራጊነት እንደምንወጣው ጥርጥር የለንም። ስለሆነም በዚህ ፈታኝና አስቸጋሪ ወቅት ቢቻል ጠላት የሆነውን ኮሮና ቫይረስ በመግደል ራሳችንንና ህዝቦችንን ለማዳን ካልተቻለ ደግሞ ራሳችንን መስዋዕት በማድረግ ይህን ጠላት በመግደል ህዝቡን ለማዳን በጋራ እንድንረባረብ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን።

የተወደዳችሁ የህክምና ባለሙያዎች፤

የተሰለፋችሁበት የህክምና ሙያ ለወገናችሁ ፈውስና መድህን አድርጎ አቁሟችኋልና ሁሌም ክብርና ኩራት ይገባችኋል። ደከመን ሰለቸን ሳትሉ የህብረተሰባችሁን ጤና ለመጠበቅ ላደረጋችሁት ሁሉ ፓርቲያችን በዚህ አጋጣሚ ምስጋናውን ያቀርባል።

ከወረርሽኙ ጋር የምናደርገው ትግል ከማንም በላይ ዛሬም የናንተን ግንባር ቀደም ተሰላፊነትና ቆራጥነት የሚጠይቅ ነው። እንደሁልጊዜው በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁና በፅናት ቆማችሁ ለወገናችሁ ጤና ዘብ እንደምትሆኑ ፅኑ እምነታችን መሆኑን እየገለፅን ወቅቱ በሚጠይቀው የቁርጠኝነት ደረጃ፣ በጀግንነት እንድትረባረቡ ጥሪያችንን እያቀረብን ፓርቲያችን ምንጊዜም ከጎናችሁ መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።

የተከበራችሁ የፀጥታ አስከባሪ ሃይሎች

ዘመናትን በዋጀ የመስዋእትነት ታሪካችሁ የሀገራችንን ልዕልናና ህልውና ጠብቃችሁ ሰላምና ደህንነትን አጎናፅፋችሁናል። ዛሬም ከፊታችን የተደቀነው ፈተና የናንተን ቆራጥ ተጋድሎና ጀግንነት ይጠይቃል። በመሆኑም በስምሪታችሁ ሁሉ በቆራጥነት በመሳተፍ ሀገራችሁንና ህዝባችሁን ከወቅታዊ አደጋ እንድትታደጉ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

የተከበራችሁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሁላችንንም የተባበረና የተቀናጀ ርብርብ ትፈልጋለች። በመሆኑም የፖለቲካ አመለካከትና ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ወረርሽኙን ለመከላከል በጋራ እንድንረባረብ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

የተከበራችሁ የሀገራችን የሚዲያና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች

ወረርሽኙን በመከላከል ተግባር በግንባር ቀደምትነት ተሰልፋችሁ በየሙያ መስካችሁ ህዝባችንን ለማስተማር፣ ለማሳወቅና ለማስተባበር እያደረጋችሁት ላለው ጥረት ፓርቲያችን አድናቆቱን ይገልጻል። ወደፊትም ወሳኝ በሆኑት የሙያ መስኮቻችሁ የተዓማኒና የትክክለኛ መረጃ ምንጭ፤ የህብረተሰባችን የግንዛቤ ማሳደጊያ፣ ማስተማሪያና መደጋገፊያ መድረክ ሆናችሁ እንድታገለግሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ውድ የሀገራችን ሕዝቦች

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደሀገር የሰነቅናቸውን ሕልሞች ሊነጥቀን የመጣ ጠላት ነው። የምናደርገው ጦርነት ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረ፣ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ያረጋገጠችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች፣ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ማዕከል የሆነች ሀገርን ለመገንባት የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ነው።

ይህንን ትግል አሸንፈን የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ሃላፊነት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ወራሪም ሆነ ወረርሽኝ ታግሎ እንጅ አሸንፎን አያውቅምና ዛሬም ይህንን ፈተና በፅናት መክተን የብልፅግና ጉዟችንን እንደምንቀጥል ፓርቲያችን ፅኑ እምነት አለው።

አንድ ሆነን ተጋግዘን እና ተረባርበን አስቸጋሪውን ጉዞ እናልፋለን፤ ወደ ብልፅግና እንሻገራለን። ስለሆነም መላው የሃገራችን ህዝቦች ሁሉንም አቅሞቻችንን አስተባብረን ወረርሽኙን በጋራ እንድንከላከል ፓርቲያችን የከበረ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል።

ሁላችንም ኮሮና ቫይረስን የሚከላከለው ሠራዊት አባላት ነን !!

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.