Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል በዓል በአፋር ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከበረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 127ኛው የአድዋ ድል “ዓድዋ፣ አንድነት፣ ጀግንነትና ፅናት” በሚል መሪ ቃል በአፋር ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቅት ተከብሯል፡፡

በአከባበር ስነ ስርዓቱ ላይ  የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት፣ የክልሉ የጸጥታ ሃይሎች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ ኢሴ አደም ባስተላለፉት መልዕክት÷የዓድዋ ድል አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰውና ውድ ህይወታቸውን ገብረው ልጆቻቸው የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ ያደረጉበት ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል።

ቀደምት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ክብሯን አስጠብቀው፣ ዳር ድንበሯን አስከብረው ሉዓላዊት ሀገር ከደምና ከአጥንት ዋጋ ከፍለው ለቀጣዩ ትውልድ አስረክበው አልፈዋልም ነው ያሉት፡፡

የዛሬው ትውልድም ከአባቶቹ የተረከበውን አደራ በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ያሳሰቡት ሃላፊው ÷አባቶቻችን በዓድዋ የተቀዳጁትን ድል በልማት አጠናክረን መቀጠል የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያውን የነፍስ ወከፍ ግዴታችን ነው ብለዋል።

ዓድዋን ስንዘክር፣ ስናስታውስ ከድሉ የምንቀስማቸውን በርካታ እሴቶችና ትምህርቶችን በየዘመኑ በመቀመር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የብልፅግና ማማ ለማሸጋገር መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከእያንዳንዳችን የምትጠብቀውን በመፈፀም ለቀጣይ ትውልድ የተሻለችና የተመቸች ሀገር ማስረከብ ይኖርብናል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.