Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ያለውጭ ጣልቃ ገብነት ውስጣዊ ችግሯን የመፍታት አቅም እንዳላት ያሳየ ነው- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ያለውጭ ጣልቃ ገብነት ውስጣዊ ችግሯን የመፍታት አቅም እንዳላት ያሳየ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ጉባኤ ላይ በአዘርባጃን ባኩ ከተማ እየተሳተፈ ነው።

አቶ ደመቀ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር÷የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ያለውጭ ጣልቃ ገብነት ውስጣዊ ችግሯን የመፍታት አቅም እንዳላት ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የሚጠበቅባትን አተዋጽኦ እያበረከተች እንደምትገኝም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገለልተኛ ሀገራት መርህን በማክበር እና ለመርሑ መከበር እንደምትሰራም ነው አቶ ደመቀ የተናገሩት፡፡

የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረክ ፍትሃዊ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መርህ እንዲጠናከር ኢትዮጵያ ትሰራለች ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡

የተባበሩት መንግሥት ድርጅት መርህን በማክበር እንዲሁም የሀገራትን ሉአላዊ የግዛት አንድነት ማክበር እና በውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ያለመግባት እሴቶች ኢትዮጵያ በእጅጉ ታከብራለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ100 በላይ ሀገራት የንቅናቄው አባል አገራት ሲሆኑ ÷አዘርባጃን የወቅቱ የንቅናቄው ሊቀ መንበር ናት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.