Fana: At a Speed of Life!

127ኛው የዓድዋ ድል በዓል አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ

127ኛው የአድዋ ድል በዓል በመላ ሀገሪቱ በወጣለት ፕሮግራም መሠረት ተከብሯል። ለዚህ ስኬት አስተዋጽዖ ያደረጉትን አካላት ሁሉ መንግሥት ያመሰግናል።

127ኛው የአድዋ ድል በዓል ያለፈውን ታሪክ በሚያዘክር፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጸና፣ የሀገር ግንባታንም በሚያጠናክር መልኩ እንዲከበር መንግሥት አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል። ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻልም በሕግ በተደነገገው መሠረትና በመከላከያ ዋና ባለቤትነት እንዲከበር ተወስኖል።

የአድዋ ድል በዓል ኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ሠራዊት ሆነው ሀገራቸውን የታደጉበት ድል ነው። በዚያ ጊዜ መደበኛ ሠራዊት ባለመኖሩ ሁሉም ሕዝብ ሠራዊት ሆኖ ዘምቷል። የዚህ ታሪካዊና ሕዝባዊ ሠራዊት ታሪካዊ ወራሽ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነው። መከላከያ በዓሉን በዋናነት እንዲያከናውን የተደረገውም በዚህ ምክንያት ነው።

በዓሉ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ፣ በአድዋ ድልድይና በመስቀል አደባባይ እንዲከበር የተደረገው በምክንያት ነው። በሕግ በተደነገገው መሠረት ጠዋት በምኒልክ አደባባይ የሀገሪቱ ርእሰ ብሔር በተገኙበት ተከብሯል። በልማድ በታወቀው መሠረት ደግሞ በአድዋ ድልድይ ረፋድ ላይ የዘማቾችን ጉዞ በሚያሳይ መንገድ ተከብሯል።

ሕዝባዊና ወታደራዊ ትርዒትን በሚገባ ለማከናወን ምቹ በሚሆነው በመስቀል አደባባይ ደግሞ የሀገሪቱ ርእሰ ብሔር፣ የክልል ርእሳነ  መስተዳድር፣ የመከላከያ አዛዦች፣ የጸጥታ አባላትና ሕዝቡ በተገኘበት፣ ተከናውኗል። የመስቀል አደባባይ የተመረጠው የጥንታዊዉን ዘማቾች ጉዞና የአድዋ ዘማቾች የታሪክና የመንፈስ ወራሽ የሆነው የመከላከያ ሠራዊትን አሁናዊ ብቃት በሚያሳይ መልኩ ለማክበር አመቺ በመሆኑ ነው።

በዓሉ በብሔራዊ ደረጃ በአዲስ አበባ ቢከበርም፣ በመላ ሀገሪቱ እንደ አመቺነቱና እንደየሁኔታው በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። በዚህም ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሻገረች መሆኑን አመልክቷል።

127ኛው የአድዋ ድል በዓል ከወትሮው በላቀና ድሉን በሚመጥን መልኩ እንዲከበር የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት በቂ ዝግጅት አድርገዋል። የጸጥታ ተቋማትም የበዓሉን ድባብ የሚያውክ ነገር እንዳይፈጠር የቅድሚያ መረጃዎችን መሠረት አድርገው በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተዋል።

በበዓል አዘጋጆችና በጸጥታ አካላት ጥምረት በዓሉ በብሔራዊ ደረጃና በመላ ሀገሪቱ በታቀደለት ልክና ዓላማ ተከብሯል።

ይሁን እንጂ ይሄንን መሰል ሀገራዊ ክንውኖች እንዳይሳኩ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን የጸጥታ አካላት አስቀድሞ መረጃ ነበራቸው። በመረጃው መሠረትም ተገቢውን ጥንቃቄ እና ጥበቃ አከናውነዋል።

በተለይም በምኒልክ አደባባይ የሚደረገውን በዓል ለመረበሽ የፈለጉ አካላት ሁከት ለመቀስቀስ ሞክረው ነበር። እነዚህ አካላት የአደባባዩን በዓል መረበሽ ሲያቅታቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚደረገውን ሃይማኖታዊ በዓል ለመረበሽ ሞክረዋል።

የጸጥታ አካላት ሑከት ፈጣሪዎችን ለማስታገሥ በሚያደርጉት ጥረት በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበረው ሃይማኖታዊ በዓል ሊስተጓጎልና ለሃይማኖታዊ በዓል የመጡ  ምእመናን መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሆኖም የጸጥታ አካላት ባደረጉት ርብርብ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ የተሸረበዉን ሤራ ከሽፏ።

መንግሥት ይሄንን መሰል ተግባር  መፈጸም እንደሌለበት ያምናል።  ሁኔታውንም አጣርቶ በችግር ፈጣሪዎች ላይ ተገቢውን ርምጃ ይወስዳል።

በአጠቃላይ በዓሉ በታሰበው ደረጃና ልክ እንዲከበር ኃላፊነት ወስደው የሠሩትን ሁሉ መንግሥት ያመሰግናል። ከዘንድሮው አከባበር በተወሰዱ ትምህርቶችም ለወደፊቱ የተሻለ የበዓል አከባበር እንዲኖር መንግሥት ጥረት ያደርጋል።

የካቲት 23/2015 ዓ/ም

አዲስ አበባ

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.