Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በተከሰተ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ትላንት ምሽት በተከሰተ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

አደጋው ከምሽቱ 12:36 ሰዓት ላይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጉርድ ሾላ ንግድ ባንክ ጀርባ ነው የተከሰተው።

በእሳት አደጋው ሁለት መኖሪያ ቤቶችና 10 የንግድ ሱቆች መቃጠላቸውን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ተናግረዋል።

በተጨማሪም አንድ የእሳት አደጋ ሰራተኛን ጨምሮ በሶስት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን አቶ ንጋቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልፀዋል።

የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር 13 የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎች፣ አንድ የውሃ ቦቴ፣ ሶስት አንቡላንስና 103 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተዋል ብለዋል።

አስቀድም የተስፋፋውን የእሳት አደጋ ወደ አካባቢው ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ ባለበት መቆጣጠር መቻሉንም ጠቁመዋል።

የእሳት አደጋውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር 2:35 ሰዓት መፍጀቱን ነው ያመላክቱት።

የአደጋው መንስኤ እና የደረሰው የጉዳት መጠን እየተጣራ መሆኑንም አንስተዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.