Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ምርመራን ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ ስራውን የሚሰራው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነው።

የምርመራ ስራው በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚጀምር ሲሆን በቀን 50 ናሙናዎችን መርምሮ ውጤቱን የማሳወቅ አቅም እንደሚኖረው የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ተናግረዋል።

ለዚህ ምርመራ የሚሰማሩ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አማካኝነት ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ተቋማቱ ለምርምራ ስራው እያደረጉት ያለው ዝግጅት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር አብርሀም በላይ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተጎብኝቷል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር አብርሀም በላይ ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን እውቀት እና መሳሪያ ተጠቅመው የሀገሪቱን የምርመራ አቅም ለማስፋት የሚያስችል ስራ ላይ መሰማራታቸው አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና በበኩላቸው ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውሉ የነበሩ መሳሪያዎችን ግብአታቸውን በማሟላት እና በማሻሻል ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሚያስፈልጋት አገልግሎት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.