Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከካዛኪስታን እና ከሰርቢያ የምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከካዛኪስታን እና ከሰርቢያ የምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ።

በአዘርባጃን ባኩ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ጉባኤ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ደመቀ፥ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚኖራትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ተወያይተዋል።

የካዛኪስታን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካኔት ቱመሽ በኢትዮጵያ በመንግሥት በኩል የተካሄዱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ለውጦችን አድንቀዋል።
ካኔት ሀገራቸው በቱሪዝም እና በኢንሸስትመንት አቅሞች ላይ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በቢዝነስ ሥራዎች የተሰማሩ ባለሀብቶች በካዛኪስታን ጉብኝት እንዲያደርጉ እና ትሥሥራቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

እንዲሁም ካዛኪስታን ለተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል እንደምታመቻችም ተናግረዋል።

አቶ ደመቀ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የነበረውን ውስጣዊ ችግር ለመፍታት በሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥ በውስጥ አቅም ችግሮችን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችና ወደ ተግባር የተገባበትን ሂደት አስረድተዋል።

የሁለቱን ሀገራት የንግድ እና የቢዝነስ ትብብር በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

በተመሳሳይ አቶ ደመቀ ከሰርቢያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይቨክ ዳሴክ ጋር ባደረጉት ውይይት ፥ በሀገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ካዛኪስታን እና ሰርቢያ የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ አባል ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር በዓለም አቀፍ መድረኮች፣ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በትብብር ይሠራሉ።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.