Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት መፈጸም ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት መፈጸም በቅርቡ እንደሚጀመር ተገለጸ።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የክፍያ ስርአቱ የሚጀመርበት እና አጠቃላይ ሂደቱን በተመለከተ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ መንግስት የነዳጅ ግብይት ስርአትን ለማዘመን በርካታ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ገልጸዋል።

ለዚህም ገፊ የሆነው ምክንያት በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ እየተሸጠ በመሆኑ ነው ብለዋል።

እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ አንጻር መንግስት ከግማሽ በላይ እየደጎመ ሲያቀርብ መቆየቱንና ይህም ጫና መፍጠሩንም አንስተዋል።

የነዳጅ ሪፎርሙ አላማ ዋጋውን ወደ ትክክለኛ ዋጋ የመውሰድ፣ግብይትና ስርጭቱን ማስተካከል ዋነኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

የግብይት ስርአቱን ዲጂታላይዝ ማድረግም የሪፎርም ስራው ዋና አካል መሆኑን እስከ አሁንም 1 ሺህ 26 ማደያዎች ወደ ቴሌብር አሰራር መግባታቸውን ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት።

በቅርቡ ሙሉ በሙሉ የግብይት ስርዓቱ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው÷ የክፍያ ስርአቱ ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ አለመሆን የነዳጅ ድጎማ ስርአቱ ላይ ችግር መፍጠሩን እና ለቁጥጥርም አስቸጋሪ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይህንንም ለመፍታት የነዳጅ ግብይቱን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርአት መፈጸም አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.