Fana: At a Speed of Life!

“የታንኩ ባላባት” ሻለቃ በቀለ በረዳ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 1970 ዓ.ም የካቲት በ26ኛው ቀን በጅግጅጋ ከተማ መግቢያ ላይ በሚገኘው የካራማራ ተራራ ላይ የካራማራ ድል ተበሰረ።

ነገር ግን የወራሪው የዚያድ ባሬ ጦር በወቅቱ ቀብሪደሃር፣ ደጋቡር፣ ዋደር፣ ጎዴ፣ ምስራቅ ጋሸንና ሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶችን ለቆ አልወጣም ነበር።

ይህንን ርዝራዥ ሀይል የማስወጣቱ ዘመቻም እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ የቀጠለ ነው።

በእናት ሀገር ፍቅር ልቡ የነደደው ሻለቃ በቀለ በረዳ÷ ምንም እንኳ በካራማራ ጦርነት ባይሳተፍም የተቀረውን ወራሪ ድባቅ በመምታቱ ረገድ ግንባር ቀደም ሆኗል።

በቀድሞ ከፋ ክፍለ ሀገር በዋካ አውራጃ ቶጫ በተባለ ቦታ የተወለደው ሻለቃ በቀለ በረዳ በቶጫ፣ ዋካና ጅማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህት ቤቶች ከ1 እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርቱን ተከታትሏል።

የ12ኛ ክፍል የመንፈቅ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም ነበር በ1969 ዓ.ም አጋማሽ የእናት ሀገር ጥሪ የታወጀው፤ለጥያቄው አሻፈረኝ ያላለው ሻለቃ በቀለ በረዳም ትምህርቱን ትቶ ሆለታ ጦር ማሰልጠኛ ገባ።

ሻለቃ በቀለ ስልጠናውን እንዳበቃ በ1971 ዓ.ም ከአዋሽ አርባ አንድ ሻለቃ ጦር ይዞ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ዘመተ።
በዚያም ታላቅ ጀግንነትና ጀብዱን ፈፀመ፤ በቀጣዩ 1971 ዓ.ም ጦሩን ይዞ ከቀብሪደሃር ወደ ዋደር በመሄድ ድንበር ለማስከበር ቻለ፤ነገር ግን ወራሪው ጦር በ1972 ዓ.ም ሀይሉን አበርትቶ በመምጣት ዋደርን ተቆጣጠረ።

በወቅቱ በዋደር የነበረው የኢትዮጵያ ጦር አንድ ሻለቃ ኮማንዶና 23ኛ ክፍለ ጦር ብቻ ነበረ፤አንድ መድፍ የነበረው ሻንበሉ ከተደራቢ እግረኛ ጦር በቀር የሚረዳው ሌላ ሀይል ስላልነበረ ከጠላት ጦር ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ የሰማይና ምድር ያህል ነበር።

በአንፃሩ ወራሪው ሀይል 5 ክፍለ ጦር አደራጅቶ ለበቀል ተመልሷል።

ጦሩ በገላዲና፣ በሽላቦ፣ በምስራቅ ጋሻን መስመር የተደራጀ ማጥቃት ጀመረ። በወቅቱ አንድ ሻንበል ይመራ የነበረው ሻለቃ በቀለ በረዳ ሠራዊቱን ይዞ የመከላከል እርምጃ ወሰደ።

ፋሺሽት ዚያድ ባሬ በ5 ክፍለ ጦር የከፈተውን ጥቃት በጋራ ይከላከላል የነበረው የሻለቃ በቀለ በረዳ መድፈኛ ሻንበልም ድጋፍ ከኢትዮጲያ አየር ሀይል ይሰጠው እንጂ ለመቁጠር አዳጋች የነበረውን የጠላት ሀይል ሰብሮ ለመግባት አዳጋች ሆነበት።

ሻንበሉ በቂ የመሳሪያና የሰው ሀይል ስላልነበረው ከቦታ ቦታ በመዘወር የመከለል እርምጃውን ቀጠለ፤ይህም ጥረቱ በሻለቃ በቀለ በረዳ ተዋግቶ አዋጊነት ሚና በሐምሌ 1972 ዓ.ም ፍሬ አፍርቶ ዋደር ከጠላት ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጣች።

ሻለቃ በቀለ በረዳ ግንባር ቀደም በሆነበት በዚህ ሻንበል ከበርካሌ እስከ ሻቡወላ፣ ከሻቡወላ እስከ አባተሌ፣ ከአባተሌ እስከ ወልወል ድረስ በመንቀሳቀስ ሠራዊቱ በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ወኔ ተዋግቷል፤ታላላቅ ገድላትን እየፈፀመም ጦሩ ወደፊት ገፋ።

በቀጣዩ 1973 ዓ.ም በሻለቃ በቀለ በረዳ የሚመራው ሻንበል የሚገኝበት ክፍለ ጦር ሙሉ ለሙሉ የጠላትን ጦር ከሀገር ለማስወጣት ይቻለው ዘንድ በወቅቱ ለነበሩት ለሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ጥያቄ አቀረበ።

በዚህ የተደሰቱት ርዕሰ ብሔሩ ኮለኔል መንግሥቱ ሀይለማርያምም በወቅቱ ግንባር ድረስ በመገኘት ፍቃዱን ሰጡ፤ዘመቻውም ተጀመረ።

ሻለቃ በቀለ በረዳ በሜሪካለብ ግንባር ጦርነቱን ወደፊት መሩት፤ በየመንገዱ የነበረውን የጠላት ሀይል እያፀዱ በአንድ ቀን ውጊያ ገላዲን ሙሉ በሙሉ ነፃ አወጡ።

ነገር ግን ከገላዲን በኋላ ያሉ ዶዶብ፣ ቦህና ቦዛን የተባሉት የኢትዮጵያ ግዛቶች በጠላት ቁጥጥር ስር ነበሩ፤ ግዛቶቹ በ1970 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ሆኑ።

ይሁን እንጂ የጠላት ጦር ወደ ደጎብ መሬት ዘልቆ መግባቱን አልተወም ነበር፤ ለዚህ ድፍረቱ ምላሽ የሰጠው የሻንበል በቀለ በረዳ ጦርም በመልሶ ማጥቃት ወራሪውን በሚገባው ቋንቋ አናገረው። ደጓብን በመቆጣጠር የጠላት ቀጠና በመግባት ምርኮኛ ይዞ ተመለሰ።

ሻለቃ በቀለ በረዳ በ1974 ዓ.ም ለትምህርት ተፈልጎ በመምሪያ መኮንንነት ለመሰልጠን በድጋሚ ሆለታ ጦር ትምህርት ቤት ገባ፤ ከ6 ወራት ስልጠና በኋላ ሻለቃ በቀለ በ30/9/1974 ዓ.ም ዋርደን ደረሰ። ነገር ግን የጠላት ሀይል ችላቦ ላይ ከፍተኛ ጥቃት በመሰንዘሩ ሠራዊቱ ካንፕ ሳይደርስ መንገድ ላይ ተዘጋጅቶ እየጠበቀው የነበረውን አንድ ሻንበል ጦር እየመራ ወደ ግንባር ዘመተ።

በችላቦ አቅጣጫ 8ኛ ክፍለ ጦር ይገኝ ነበርና ከአንድ ቀን ጉዞ በኋላ የሻለቃ በቀለ አንድ ሻንበል ጦር እዛ ደረሰ፤በዛኑ ዕለት ስትራቴጂ የነደፉት የኢትዮጵያ ጀግኖች ሌሊቱን ቦታ ይዘው በማደር በማለዳው ስፍራውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ።

ድሉ ለሌላ ድል የሚያነሳሳ ሆነ፤ሻለቃ በቀለ በረዳም በ2/10/1974 ዓ.ም መንቻር በሚባል ቦታ ከ96ኛ ክፍለ ጦር ጋር ቅንጅት ፈጥሮ ጠላትን ያርበደብደው ጀመር። ነበልባሉ የኢትዮጲያጦር በወሰደው እርምጃ በለንበብ የምትባል ግዛት ነፃ ሆነች።

በነጋታው በ3/10/1974 ዓ.ም ወራሪው ድጋሚ ሀይል አደራጅቶ ከተጨማሪ ብርጌድ ጦር ጋር መጣ። በወቅቱ አንድ ሻንበል እየመራ የነበረው ሻለቃ በቀለ በረዳ አንድ ብርጌድ እግረኛ ጦርና ከባድ መሣሪያዎችን ከታጠቀ የጠላት ጦር ጋር ተፋጠጠ።

ታንከኛው ሻንበል ጦር ከኋላ የወገን ጦር እዳለ በማሰብና ከፊት ሜዳማው የኦጋዴን መሬት ለጠላት አመቺ መሆኑን በማሰብ በሻለቃ በቀለ አመራር ሰጪነት ለማጥቃት የጠላትን ጦርን መሀል ሰብሮ ገባ።

ሻለቃ በቀለ በረዳ ሰብሮ ከገባ በኋላ 3 ታንኮች ከበቡት፤የሻንበሉ ታንክ አዛዥ እንደመሆኑ መጠንም እነዚህ ሶስት የጠላት ታንኮች በክላሽ መፋለም አሊያ ማፈግፈግ ምርጫው ሆነ፤ እሱ በወቅቱ ግን በጀግንነት መዋጋትን መረጠ።

ታንክ አዛዥ የነበረው ጀግናው ሻለቃ በቀለ በረዳ እርሱ ያለበት ታንክ በሶስት የጠላት ታንክ ተከበበ። የታንኩ ሰንሰለት ማጠንጠኛ በመመታቱም ከጠላት ጋር በክላሽ መፉለም ግድ ሆነበት ትንታጉ ሻለቃ በቀለ በሶስቱ ታንኮች ላይ የነበሩ የጠላት ተኳሾችን በብርሃን ፍጥነት አሰናበታቸው። አንደኛው ታንክ ላይ ዘሎ በመውጣትም ሹፌሩንና ሌሎች አባላቶቹን በመግደል ታንኩን ሲማርክ ሁለቱ ታንኮች ተፈተለኩ።

መቶ አለቃ ሰለሞን የተባሉ ሌላ ግለሰብ ሻለቃ በቀለ የማረከውን ታንክ እንዲረከቡ በሬዲዮ ጠራቸው፤ እርሳቸው ከተረከቡ በኋላ እርሱ ግን ወዳመለጡት ሁለት ታንኮች ክላሹን አንግቦ ተንቀሳቀሰ። ወኔ ተላብሶ በመዋጋት ታንክ ተኳሽ፣ አዛዥና ሹፌሩን በመግደል ሁለተኛውን ታንክ ለመቆጣጠር ቻለ።

ይህም ታንክ በወቅቱ የታንክ እጥረት ለነበረበት ለወገን 8ኛ ክፍለ ጦር በስጦታ ተበረከተ፤ጠላትም በለንበምና መተባን የተባሉ የራሱን መሬት ትቶ እግሬ አውጪኝ አለ፤ የወገን ጦርም ወራሪውን የዚያድ ባሬ ጦር ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንዳይመለስ አድርጎ የሞቃዲሾ መንገድን አሳይቶት ተመለሠ።

1977 ዓ.ም የተደረገው የኢሰፓ ጉባዔ ሻለቃ በቀለ በረዳን አክብሯቸዋል፤ ጉባኤው በወቅቱ በኢትዮጵያ ከሚሰጡት የክብር ሜዳልያዎች መካከል በደረጃው ሁለተኛው የሆነውን “የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳል” አበርክቶላቸዋል።
ሽልማቱንም ከኮለኔል መንግስቱ ሀይለማርያም እጅ ተረክበዋል።

በኢዮናዳብ አንዱዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.