Fana: At a Speed of Life!

‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንዲሰማራ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የንግድ ተቋም ‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እና ሌሎች የፋይናንስ መስኮች ላይ እንዲሰማራ ጥሪ ቀረበ፡፡

‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ የኢነርጂ መሰረተ ልማትን ጨምሮ በዘላቂ የፋይናንስ ዘርፎች ላይ የሚሰራ የንግድ ተቋም ነው ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ መቀመጫውን ሀንጋሪ ካደረገው ተቋም ጥምር መስራች ዶ/ር ፒተር ናጊ ጋር በኳታር ዶሃ ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ በዶሃ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን÷ምክክሩም ‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ በኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ ላይ በሽርክና በሚሰራበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ለተቋሙ ጥምር መስራች ዶ/ር ፒተር ናጊ በኢትዮጵያ የኢንቨሰትመንት እድሎች በተለይም በታዳሽ ኃይል እና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘርፎች ያሉ አማራጮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግስት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ በባንክ እና ፋይናንስ ዘርፍ ላይ የውጭ ባለሀብቶች  እንዲሳተፉ ለማድረግ እና ለካፒታል ገበያ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ውይይቱ ‘ካፒታል ኢኩዊሊብረም’ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋም ከመንግስት ጋር በመንግስት እና በግል አጋርነት ማዕቀፍ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሌላ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ በኳታር ዶሃ እየተገነባ ያለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ጎብኝተዋል።

የቤተ ክርስቲያኗ ግንባታ በ1 ሺህ 846 ሜትር ስኩዌር ላይ ያረፈ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷የግንባታው መሬት ከኳታር መንግስት የተሰጠ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.