Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
 
በሚኒስቴሩ የመድሃኒትና ህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት መሪ ስራ አስፈጻሚ ረጋሳ ባይሳ÷በትግራይ ክልል ሁሉም አካባቢዎች በግጭቱ የተጎዱ የጤና ተቋማትን ዳግም ስራ ለማስጀመር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሆስፒታሎች እና ጤና ጠቢያዎች ባሉበት ሁኔታ ላይ ዳግም ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን አንስተዋል፡፡
 
ለመሰረታዊ የጤና አገልገግሎት የሚውሉ አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶች በክልሉ እየተሰራጩ መሆኑንም አቶ ረጋሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
 
በመቀሌ እና አካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎች እና ጤና ተቋማት ባሉበት ሁኔታ ዳግም አገልግሎት እንዲስጡ ለማድረግም ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
በቅርቡም የጤናሚኒቴር ልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ አቅንቶ መቀሌ እና አካባቢው የሚገኙ ጤና ተቋማት አሁን ላይ ያሉበትን ሁኔታ መገምገሙን ጠቁመዋል፡
 
በዚህም ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው መመልከት መቻሉን ጠቁመው÷አስቸኳይ ህክምናዎች በሚኒስቴሩ እና አጋር አካላት ትብብር እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው ለነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት እንዲችሉም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
ይሁን እንጂ በግጭቱ ሳቢያ ጤና ተቋማቱ የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የፋይናንስ እጥረት መኖሩን ነው ያመላከቱት፡፡
 
ስለሆነም የመንግስት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች፣ዳያስፖራዎች እና የሰብዓዊ ተራድኦ ድርጅቶች በትግራይ ክልል የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.