Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ተከስቶ የቆየውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ ነበሩ – አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ ተከስቶ የቆየውን የጸጥታ ችግር በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የቤኒሻንጉል ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለፁ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክርቤት የ5ኛ ዓመት 8ኛ የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው የክልሉን የሥድሥት ወራት አፈጻጸም ያቀረቡት ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፥ ባለፉት 6 ወራት በክልሉ ለነበረው የጸጥታ ችግር መፍትሔ ከመስጠት ባለፈ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት ተከስቶ የቆየውን የጸጥታ ችግር በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩም አብራርተዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ከጉህዴን እና ከቤህነን ቡድኖች ጋር የደረሠውን የሠላም ስምምነት ተከትሎ በሠላም የተመለሱ በርካታ ወጣቶች ስልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉንም ነው የተናገሩት።

በጸጥታ ችግሩ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ-ለማቋቋም እና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ-የመገንባት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በጸጥታ ችግሩ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ 62 ትምህርት ቤቶች፣ 1 ጤና ጣቢያ፣ 60 ጤና ኬላዎች፣ 906 የውኃ ተቋማት ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ጠቁመዋል።

በክልሉ ትምህርት አቋርጠው የነበሩ 63 ሺህ 474 ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መመለሳቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.