Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተሰራ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከ6 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መሰራቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎችና የገጠር ቀበሌዎች ህዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር በተሰራው የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት መጨመሩ ተገልጿል።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ፥ በተያዘው ዓመት በሁሉም የክልሉ ዞኖች በሚባል መልኩ አርሶአደሩንና ባለሙያውን በማሰልጠን ከ6 ሺህ በላይ ተፋሰሶች እየለሙ ነው።

በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአፈር እጥበትን በመከላከል ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ በክልሉ ያለውን የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት በመጨመር ለበጋ መስኖ ስራ ትልቅ አቅም መፍጠር መቻሉንም ኃላፊው ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተፋሰስና የውሃ ዕቀባ ስራም የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የደረቁ ወንዞችና ጅረቶች እንዲመለሱና የተፋሰስ ስራ ውጤት በሆነው የአረንጓዴ አሻራ ስራም ብዙዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም ነው የጠቀሱት።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ለ60 ቀናት የሚቆይ የተፋሰስ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

አበአጠቃላይ በክልሉ በዘንድሮው ዓመት ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በመራኦል ከድር

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.