Fana: At a Speed of Life!

ዶላር በማባዛት ትርፋማ እናደርጋለን በሚል ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ያጭበረበሩ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዶላር በማጠብና በማባዛት ትርፋማ መሆን ትችያለሽ በማለት አንድን ግለሰብ በማታለል ከ5 ሚሊየን በላይ ጥሬ ብር ተቀብለው ተሰውረዋል የተባሉ ሁለት ተከሳሾች እስከ 4 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 1ኛ አርቲዲ ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ 1ኛ ተከሳሽ ታዬ ፀጋዬ እና ወንድ ልጃቸው የሆነው ቢኒያም ታዬ ሲሆኑ፥ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ በመተላለፍ የማታለል ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው በ2013 ዓ.ም የተከሰሱ ናቸው።

1ኛ ተከሳሽ ቆንጂት መስፍን የተባለችን የግል ተበዳይ ግለሰብ ጋር ስልክ በመደወል ለክርስቲያን የሚሆን ትርፋማ የሚያደርግሽ ስራ አግንቼልሻለው በማለት በውሸት ማሳመናቸው በክሱ ተመላክቷል።

ተከሳሾቹ ሶስት አፍሪካዊ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ጋር በመሆን የዶላር ማጠቢያ ዱቄት መሰል ኬሚካል ዲፕሎማት በሆኑ ግለሰቦች ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በካርጎ የሚገባ ነው በማለት ለኬሚካል ማስመጫ በሚል በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ጉርድ ሾላ ሴንቸሪ ሞል አካባቢ ሐምሌ 1 እና ሐምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ከግል ተበዳይ አጠቃላይ 5 ሚሊየን ብር በማታለል መቀበላቸው በክሱ ተጠቅሷል።

ሐምሌ 6 ቀን ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ የግል ተበዳይ ጋር በመገናኘት ኬሚካሉ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ እንደሆነ በመንገር እና ለላቦራቶሪ ማስፈተሻ በሚል 182 ሺህ ብር የተቀበላት መሆኑ በክሱ ተገልጿል።

በድጋሚ ይኼው 1ኛ ተከሳሽ ኬሚካሉን በላቦራቶሪ የሞከረችው ልጅ ለሻይ ያስፈልጋታል በማለት 40 ሺህ ብር በመቀበል እንዲሁም ከ3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ያሉ ተከሳሾች የታሰሩ በመሆኑ ወደ ውጭ ሀገር ተመልሰው እንዳይላኩ በሚል እና ወደ ውጪ ሀገር የሄዱ በመሆኑ ወረቀት አስተካክሎ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ አጠቃላይ 220 ሺህ ብር ከግል ተበዳይ የተቀበለ መሆኑ በክሱ ተዘርዝሯል።

በጠቃላይ 5 ሚሊየን 503 ሺህ ብር ከግል ተበዳይ በማታለል ገንዘብ ተቀብለው የተሰወሩ መሆኑ ተጠቅሶ በአታላይነት ወንጀል ተከሰዋል።

በ2ኛ ክስ ደግሞ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት በመሄድ ወንጀሉን እንዳታጋልጥ በማሰብ ኬሚካሉ እንዳይጎዳሽ መርፌ መወጋት አለብሽ በማለት 5ኛ ተከሳሽ ጥቁር ፈሳሽ በመርፌ በመያዝ ሊወጋት ሲል የግል ተበዳይ አምልጣ በሩን ከፍታ ጩኸት በማሰማት በአካባቢው የነበረ ሰው ደርሶ ግለሰቧ መትረፏንና ተከሳሾቹም ሮጠው ማምለጣቸው ተጠቅሶ በግድያ ሙከራ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ወንጀሉን አልፈጸምንም ብለው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ የፍትህ ሚኒስቴር ቦሌ ምድብ ዐቃቤ ህግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ከአራት በላይ ምስክሮችን በተለያዩ ቀናቶች አቅርቦ አሰምቷል።

የዐቃቤ ህግ የምስክር ቃልን ፍርድ ቤቱ መርምሮ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናቶች የመከላከያ ማስረጃ ያቀረቡ ቢሆንም የዐቃቤ ህግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ዐቃቤ ህግም ተከሳሾቹ ቅጣቱ ከብዶ በጽኑ እስራት እንዲቀጡ የቅጣት ማክበጃ አስተያየት አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የ1ኛ ተከሳሽ በጠበቃው አማካኝነት ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ በሙሉ ውድቅ በማድረግ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ በሚመለከት ብቻ አንድ ማቅለያ በመያዝ በዕርከን 19 መነሻ መሰረት በ4 አመት ጽኑ እስራትና በ6 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኗል።

2ኛ ተከሳሽ ልጃቸውን በሚመለከት ግን የበጎ አድራጎት እና ለህዳሴ ግድብ ያበረከተው ድጋፍ ጨምሮ አራት የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በዕርከን 7 መነሻ በ6 ወራት ቀላል እስራት እንዲቀጣ በዛሬው ቀጠሮ ተወስኗል።

ፍርድ ቤቱ በህመም ምክንያት ዛሬ ችሎት አልቀረቡም የተባሉትን 1ኛ ተከሳሽን ፖሊስ አስሮ ለማረሚያ ቤት በማስረከብ ሁለቱም ተከሳሾች እስራቱን እንዲፈጽሙ እንዲያደርግ ታዟል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.