Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ከቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው በቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀመንበር ሊ ዚያንግ ከተመራው የልኡካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸውም በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ባለው የኢኮኖሚ ትብብር እና በቀጣይ በሚከናወነው የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ መክረዋል፡፡
 
ወ/ሮ ሰመሪታ ÷ የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን በኢትዮጵያ በሃይል ማመንጫና በመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታዎች ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየ ግዙፍ የቻይና ኩባንያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ ከዚህ ግዙፍ ተቋም እና ከሌሎች የቻይና ባለሃብቶች ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አስረድተዋል፡፡
 
ሊ ዚያንግ በበኩላቸው÷ ቡድኑ በኢትዮጵያ የተከዜ ሃይል ማመንጫን፣ የፊንጫ አመርቲ ነሽ ሃይል ማመንጫን፣ ገናሌ ዳዋ 3 ሃይል ማመንጫንና የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን ተናግረዋል፡፡
 
ቡድኑ በቀጣይነትም በኢትዮጵያ በማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሁም በታዳሽ ሃይሎች ኢንቨስትመንት የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አመላክተዋል፡፡
 
የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ከቻይና ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል የሚጠቀስና በርካታ ቢሊየን ዶላር ካፒታል ያለው የኢንቨስትመንት ተቋም መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
 
ከሃይል ማመንጫ ግንባታዎች በተጨማሪ በመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች፣ በማምረቻ፣ በቤቶች ግንባታና በሌሎች በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራ ተቋም መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.