Fana: At a Speed of Life!

በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ እስካሁን 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት መልማቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ እስካሁን 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት መልማቱን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ ያለው የተፋሰስ ልማት ስራ በ2015 ዓ.ም ማህበረሰብ አቀፍ የተፋሰስ ልማት ስራ ንቅናቄ በተያዘለት እቅድ በሁሉም ክልሎች በስፋት መሰራቱን ነው ሚኒስቴሩ የገለፀው፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ÷ በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ከ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የተፋሰስ ልማት ስራው በዋናነት በስነ-አካላዊ ስራ ላይ ያተኮረ ሲሆን ቀጣይ ለሚሰሩ ስነ-ህይወታዊ የተፋሰስ ልማት ስራዎች መደላድልን የፈጠረ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል፡፡

አዳዲስ ተፋሰሶችን ከመስራት ጎን ለጎንም የነባር ተፋሰሶች ጥገናና እድሳት ስራ በስፋት መሰራቱንም ነው የተናገሩት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው አመት ከ30 ሺህ በላይ ተፋሰሶች ለማልማት እቅድ በመያዝና ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ለመከለል ታስቦ እስካሁን ከ570 ሺህ ሄክታር በላይ በተፋሰስ ልማት መከለል ተችሏል ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተሰሩት የተፋሰስ ልማት ስራዎች ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.