Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 22 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከጀርመን ልማት ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ 22 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው÷ ባንኩ ድጋፉን ያደረገው ከጀርመን ልማት ባንክ ባገኘው የ15 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘው ድጋፍም 79 ትራክተሮች ተገዝተው ለአርሶ አደሮች እንደሚያከፋፍሉ ጠቅሰው÷ ከዚህ ውስጥ ዛሬ 22 ትራክተሮችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ትራክተሮቹ በባንኩ “20 በ 80” የቁጠባ ዘዴ ለቆጠቡ አርሶ አደሮች መሰጠታቸውን ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ ቀደም የድጋፉ አካል የሆኑ 9 ትራክተሮች ተገዝተው ለአርሶ አደሮች መከፋፈላቸውን አስታውሰው÷ የቀሪ 48 ትራክተሮች ግዥ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ትራክተሮቹ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ እንዲስፋፋ በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የተያዘውን የልማት ጉዞ ለማፋጠን እንደሚያግዙም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የግብርና ዘርፉን በማገዝ ረገድ ከዚህ በፊት 300 ትራክተሮችና 100 ኮንባይነሮች ግዥ በመፈጸም ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረጉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.