Fana: At a Speed of Life!

ተወዳዳሪ አምራች ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በተኪ ምርቶች ላይ የሚሰማሩ ተወዳዳሪ አምራች ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር የሚያስችል የ10 ዓመት ዕቅድ ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርጓል፡፡

በመድረኩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች፣ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ÷ ተቋሙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲጠናከሩና እንዲስፋፉ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አዲሱ ፍኖተ ካርታ ከጀርመን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው አምራች ኢንተርፕራይዞች ተወዳዳሪ እና በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እዲያመርቱ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ተቋሙ የማምረቻ ማዕከላትን የመገንባት፣ የማስተዳደርና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ስራዎችን እንዲሰጥ ተጨማሪ ተልዕኮ የተሰጠው በመሆኑ ፍኖተ ካርታው ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

የዘርፉ ልማት የሚፈልገውን የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ፣ የማምረቻ ቦታ፣ የስልጠና፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የገበያ ትስስርና መሰል ድጋፎችን በተገቢው ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስችልም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እንዲሆኑ እና በወጪ ምርት ላይ በስፋት እንዲሰማሩ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫዎት ጠቁመዋል፡፡

እቅዱ ኢትዮጵያ በዘርፉ አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣይ መተግበር ያለባቸውን አቅጣጫዎች ማስቀመጡንም ገልጸዋል፡፡

ለፍኖተ ካርታው ውጤታማነት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስፈላጊ ሃሳቦችን በማካተት ተጠናቆ በዛሬው ዕለት ይፋ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.