Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የልማት ስኬቶቿን በተመድ ዓለምአቀፍ የአዳጊ ሀገራት ጉባዔ ላይ አካፈለች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸውን የልማት ስኬቶች በ5ኛው የተመድ ዓለምአቀፍ የአዳጊ ሀገራት ጉባዔ ላይ አካፍላለች፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሠፋ በኳታር ዶሃ እየተካሄደ ባለው እና በአዳጊ ሀገራት ላይ በሚመክረው 5ኛው የተመድ ጉባዔ÷ ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት፣ በስንዴ ምርታማነት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እና በተለያዩ የልማት መሥኮች ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች አቅርበዋል፡፡

አዳጊ ሀገራት ነባራዊ ሁኔታቸውን መሰረት አድርገው ሲሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ኢትዮጵያ ጥሩ ማሳያ መሆኗን አስረድተዋል፡፡

በአዳጊ ሀገራት ላይ የሚደርሱ ፈተናዎችን ለመቋቋም የዓለም አቀፍ አጋሮችን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጥ አሥፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሯ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በሥራ ላይ ያለው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ሥርዓት ትርጉም ያለው ምላሽ መሥጠት አልቻለም ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

አዳጊ ሀገራት በዓለምአቀፍ ደረጃ ለሚስተዋለው አለመረጋጋት ገፈት ቀማሽ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ አንስተዋል፡፡

ሀገራቱ በተቻለ መጠን የዓለምአቀፉን ተፅዕኖ ለመግታት እየሠሩ መሆናቸውን እና የልማት ሥራቸውን ለማስቀጠልም ጥረታቸውን እንደማያቋርጡ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ ታዳጊ ሀገራት የዓለም አቀፉን ገበያ ለመቀላቀል ፈተና እንደሆነባቸው እና ጥረታቸው ብዙም ፍሬያማ ውጤት እንዳላስገኘ አስረድተዋል።

ያደጉ ሀገራት ለታዳጊዎቹ የዕዳ እፎይታን በመስጠት የልማት እና የፋይናንስ አቅማቸውን ለማጎልበት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተመድን ዘላቂ የልማት ግቦች፣ የአፍሪካ ኅብረትን አጀንዳ 2063 እና የዶሃን የድርጊት መርሐ-ግብር ከሀገራዊ ዕቅዷ ጋር በማጣጣም ከድኅነት ለመውጣት በቁርጠኝነት እየሠራች ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.