Fana: At a Speed of Life!

ለ100 ዓመታት እንዲያገለግል ተደርጎ የተሰራው አዲሱ የዓባይ ድልድይ ግንባታ አፈፃፀም 94 በመቶ ደረሰ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህር ዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ ፕሮጀክት አፈጻጸም 94 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገልፀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በባህርዳር ከተማ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ድልድይ ጉብኝት አድርገዋል።

የድልድዩን ዋና ዋና ስራዎች በእቅዱ መሰረት ግንባታውን የማጠናቀቅ ሂደቱ በመፋጠን ላይ እንደሚገኝ ለምክር ቤት አባላት ገለፃ ተደርጎላቸዋል።

ድልድዩ ሲጠናቀቅ በሁለቱም መስመር ከሚኖረው 760 ሜትር “ግራይደር” ርዝማኔ ውስጥ 380 ሜትሩ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ፥ የድልድዩ ተሸካሚ ምሰሶዎችና ከመሬት በታች የድልድዩ የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም፥ ለድልድዩ የሚያስፈልጉ 8 ቋሚ ተሸካሚ ምሰሶዎች ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቃቸውና የተቀሩት በቅርቡ ለመጨረስ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የድልድዩ ግንባታ እየተከናወነ የሚገኘው በመንግስት በተመደበ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በጀት በቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሲሲሲ ተቋራጭነት መሆኑም ነው የተገለጸው።

አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ ለ100 ዓመታት እንዲያገለግል ተደርጎ የተሰራ ሲሆን ፥ በባህር ዳር ከተማ ከሚገኘው ነባሩ የዓባይ ወንዝ ድልድይ 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው እየተገነባ የሚገኘው።

ይህ ዘመናዊ ድልድይ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ከሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ጎን ለጎን ምቹ የሆነ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ያስችላል ተብሏል ፡፡

በ2011 ዓ/ም የተጀመረው ይህ ዘመናዊ ድልድይ የፊታችን ሰኔ 2015 የሚጠናቀቅ ሲሆን ፥ 43 ሜትር ስፋትና በአንድ ጊዜ ስድስት መኪኖችን ያሳልፋል ተብሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በባህርዳር ከተማ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ድልድይ ጎብኝተው ግንባታው በታቀደለት መሠረት እየተከናወነ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ከአማራ ብልጽግና ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.