Fana: At a Speed of Life!

የሥነ-ምግባርና ዲሲፕሊን ግድፈት አለባቸው በተባሉ 4 ዳኞች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሥነ-ምግባርና የዲሲፕሊን ግድፈት አለባቸው ባላቸው አራት ዳኞች ላይ በአብላጫ ድምጽ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

በዛሬው ዕለት ባስተላለፈው ውሳኔ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንድ ዳኛ ላይ በቀረበ ክስ መነሻ ተመርምሮ በዳኞች የሥነ-ምግባርና የዲሲፕሊን ክስ ሥነ-ሥርዓት ደንብ ቁጥር 3/2014 አንቀጽ 34(3) መሠረት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ጉባዔው በአብላጫ ድምጽ ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ ወስኗል።

ሌላ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንድ ዳኛ ደግሞ በቀረበባቸው የዲሲፒሊን ክስ መነሻ ተመርምሮ የአምስት ወር ደሞወዝ ተቀጥተው በፍቃዳቸው ያስገቡት የስራ መልቀቂያ እንዲሰጣቸው ወስኗል።

በተመሳሳይ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑ ሌላ አንድ ዳኛ በቀረበባቸው የዲሲፒሊን ክስ መነሻ ተመርምሮ ዳኛው የሁለት ወር ደሞወዝ እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡

ሌላኛው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛን በሚመለከት የአንድ ወር ደሞወዝ እንዲቀጡ በአብላጫ ድምጽ ተወስኗል፡፡

ከዳኝነት ስራቸው የተሰናበቱት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንድ ዳኛን በሚመለከት ጉባዔው የወሰነው ውሳኔ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 79 ንዑስ አንቀጽ 4 (ሐ) መሰረት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሲጸድቅ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሚሆን ከፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.