Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ንግድ ትርዒት በበርሊን እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ንግድ ትርዒት በበርሊን እየተካሄደ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በትርዒቱ ላይ÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ 28 የቱር ኦፕሬተሮች፣ ሆቴሎች እና የተወሰኑ ክልሎችን ያካተተ በቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የተመራ ልዑክ እየተሳተፈ ነው፡፡

በሚኒስቴሩ የፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ በትርዒቱ ሁሉም የዓለም ሀገራት በቱሪዝሙ ዘርፍ ያላቸውን ሥራዎች እና አቅም ያሳያሉ ብለዋል፡፡

በመድረኩ የቱር ኦፕሬተሮችን ጨምሮ በቱሪዝሙ ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ባለሃብቶች የተገኙበት  ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያም ያላትን ሁሉ የማስተዋወቅ እና የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ ታከናውናለች ነው ያሉት፡፡

እስከ ሐሙስ ከሚቆው ትርዒት ባሻገር የጎንዮሽ ውይይቶች እና ሌሎች መለስተኛ ጉባዔዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል ሲሉ ሰላማዊት ዳዊት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ናሲሴ ከበርካታ የዓለም ሀገራት የጉዞ እና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ኢትዮጵያን ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት በምርጥ መዳረሻነት ደረጃ ለማስተዋወቅ እና በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.