Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ መንግስት እና በቼክ ሪፐብሊክ የሁለትዮሽ ትብብር ላይ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ መንግስት እና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርና እና የውሃ ዘርፍ ላይ ባተኮረ አዲስ የትብብር ማዕቀፍ ላይ ምክክር ተካሄደ።

ውይይቱ የኢትዮጵያን ቀጣይ የልማት እቅድ እና የወደፊት እይታን እንዲሁም በቀጣይ በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚደረገው የልማት ትብብር የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከስምምነት ለመድረስ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በምክክር መድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰውን ጨምሮ የግብርና ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተወካዮች ተገኝተዋል።

በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር÷ ቼክ ለጂኦሎጂካል እና ሃይድሮጂኦሎጂካል ካርታ ማጠናቀቂያ ያደረገችው አስተዋፅኦን የተመለከተ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
በእቅድና ልማት ሚኒስቴር በኩል ደግሞ የ10 አመት የልማት እቅድ የትግበራ ስትራቴጂዎች ላይ አጭር ገለፃም ተደርጓል።

በግብርናው ዘርፍ ወጣቶችን ለመደገፍ፣ የምግብ እሴት ሰንሰለትን በማስተዋወቅ እና መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ለሁለቱ ሴክተሮች ቅድሚያ እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነትም ተደርሷል።

የቼክ ሪፐብሊክ የልዑካን ቡድን በቼክ ኤይድ የአፍሪካ ፕሮግራሞች ኃላፊ ማርቲን ሴፍር እና የቼክ ኤምባሲ የትብብር ምክትል ኃላፊ ካትሪና ማኖቫ የተመራ ነው።

በልማት ትብብር ማዕቀፍ (ኦዲኤ) ውስጥ ቼክ ሪፐብሊክ ከፈረንጆቹ 2001 ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እየሰራች እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ ኢትዮጵያ በቼክ ልማት ትብብር ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሀገሮች አንዷ መሆኗም ተጠቅሷል።

በደቡብ እና በሲዳማ ክልሎች እየተተገበሩ ባሉ መርሃ ግብሮች እና ፕሮጀክቶች ቼክ ሪፐብሊክ ለኢትዮጵያ በውሃ፣ በግብርና፣ በመሬት አስተዳደር እና በጂኦሎጂካል ዘርፎች ድጋፍ ማድረጓን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.