Fana: At a Speed of Life!

አቢሲኒያ ባንክ ለሴት ስራ ፈጣሪ ተወዳዳሪዎች ያለ መያዣና በአነስተኛ ወለድ ምጣኔ ብድር ማዘጋጀቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አቢሲኒያ ባንክ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ ለ50 ሴት ስራ ፈጣሪ ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው 500 ሺህ ብር ያለ መያዣ እና በአነስተኛ ወለድ ምጣኔ የብድር አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡

ባንኩ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ ‘እችላለሁ’ በሚል መሪ ሐሳብ የሴቶች የተሰጥኦ ውድድር በዛሬው ዕለት አስጀምሯል።

ለሥራ ፈጣሪ እና በሙዚቃ እንዲሁም በግጥም ልዩ ተሰጥኦ ላላቸው ሴቶች ነው ባንኩ ሽልማት እና በአነስተኛ ወለድ ምጣኔ ብድር ያዘጋጀው፡፡

በዚሁ መሰረት የሚዚቃ እና ግጥም ተሰጥኦ ያላቸው ተወዳዳሪዎች በባለሙያ እና በማኅበራዊ ሚዲያ በሚሰጥ የሕዝብ ድምጽ የሚለዩ አሸናፊዎች እንደሚሸለሙ ተገልጿል።

ተወዳዳሪዎችም ከ3 ደቂቃ ያልበለጠ የሙዚቃ ስራ እና ከ20 መስመር ያልበለጠ ስንኝ በባንኩ ማህበራዊ ገጽ ይፋ በሚደረገው የቴሌግራም አድራሻ መላክ ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡

የሽልማት መጠኑም÷ አንደኛ ለወጣ 100 ሺህ ብር፣ 2ኛ ለወጣ 60 ሺህ ብር እና 3ኛ ለሚወጣ 30 ሺህ ብር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል ስራ ፈጣሪ ሴቶችን ለማበረታታ 50 ሴት ስራ ፈጣሪ ተወዳዳሪዎችን በአነስተኛ የወለድ ምጣኔና ካለመያዣ ለእያንዳንዳቸው 500 ሺህ ብር በድምሩ 25 ሚሊየን ብር የብድር አገልግሎት ማዘጋጀቱን ባንኩ አስታውቋል።

በስራ ፈጠራ መወዳደር ፍላጎት ያላቸው እና መስፈርቱን የሚያሟሉ ስራ ፈጣሪ ሴቶች አቅራቢያቸው ባሉ ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ቀናት በአካል በመቅረብ ጥያቄያቸውን በፅሁፍ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ተገልጿል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.