Fana: At a Speed of Life!

በሴት የሰራዊት አባላት የታየው ጀግንነት ወጣት ሴት የፖሊስ ኦፊሰሮች ወደ ፌደራል ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ግንዛቤ ፈጥሯል – ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴት የሰራዊት አባላት የታየው ጀግንነት እና ቆራጥነት ወጣት ሴት የፖሊስ ኦፊሰሮችን ወደ ፌደራል ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ግንዛቤ ፈጥሯል ሲሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን አስመልክቶ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ለሴት አባላቱ እውቅና ሰጥቷል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ÷ሴት የኮሚሽኑ አባላት ለሀገር በታማኝነት እና ጀግንነት መቆምን በተለያዩ ግዳጆች በተግባር አስመስክረዋል ብለዋል፡፡

ይህ ጀግንነትና ቆራጥነትም በሌሎች የተቋሙ የስራ ዘርፎች እንዲተገበር ነው ኮሚሽነሩ የጠየቁት፡፡

በመርሐ ግብሩ በተለያዩ ግዳጆች የሀገራቸውን ህልውና በማስጠበቅ ስራ ጉዳት ለደረሰባቸው አባላት የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ከዚህ በፊት የፖሊስ ሆስፒታል 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ የተሸለሙት የአንገት ሃብል በግዳጅ ወቅት ለቆሰለች ሴት የሰራዊት አባል አበርክተዋል።

በመርሐ ግብሩ በተለያዩ ግዳጆች የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሶስት ሴት የሰራዊቱ አባላት የሰው ሰራሽ አካል በነጻ ለማዘጋጀት የሰው ሰራሽ አካል ባለሙያው አቶ ሰለሞን አማረ ቃል ገብተዋል።

በቀጣይም ለሰራዊቱ መሰል ድጋፍ እንደሚደረግ ነው የተገለጸው፡፡

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.