Fana: At a Speed of Life!

የሴቶች ቀን በዓመት አንድ ቀን የሚታወስ ሳይሆን የ365 ቀናት ሥራ መሆን አለበት – ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የ2015 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም “በመላው ሀገራችንና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ሴቶች እንኳን ለዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በደህና አደረሰን” ብለዋል።

ሁልጊዜም እንደምለው የሴቶች ቀን በዓመት አንድ ቀን የሚታወስ ሳይሆን የ365 ቀናት ሥራ መሆን አለበት ያሉት ፕሬዚዳንቷ ያለፍነውን፣ እየኖርን ያለነውንና የወደፊቱን ከሴቶች እኩልነት፣ ተጠቃሚነት ከሰው ልጅ መብት አንጻር እንድንቃኝ አስታዋሻችን፤ የማንቂያ ደወላችን ነው ብለዋል፡፡

በሴቶች ላይ ከሚደርሰው የችግር አዙሪት ለመውጣት ቁልፍ ጉዳይ የሴቶች መደራጀት ጠቅሰው፣ የመብት ትግል የተናጠል ትግል ስላልሆነ ሴቶች ጠንካራ የጋራ አጀንዳ ሊይዙ ይገባል፡፡

የሴቶች አጀንዳ የሕዝብ ጉዳይ እንዲሆን የሚሰራ፣ መፍትሔ የሚያፈላልግ፣ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ እውቀትና ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ለዚህ ዓላማ የሚያስተባብር ጠንካራ ማህበር እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡

ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለንን ትስስር ለማጠናከር ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተው “የአፍሪካ ሴት መሪዎች ጥምረት የኢትዮጵያን ቅርንጫፍ ማጠናከርና የልምድ ልውውጦችን ማጎልበት ይጠበቅብናልም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፡፡

ይህንን የሴቶች ወር በማስመልከት ያለፈውን እንድንገመግም፣ የዛሬውን በርትተን እንድንሠራና የወደፊቱን እንድናቅድ  ቆም ብለን እንድናስብ ለሁሉም  አደራ ማለት እፈልጋለሁም ብለዋል በመልዕክታቸው።

የምንገነባት ኢትዮጵያ ሴቶችና ታዳጊ ሴት ልጆች ሴት በመሆናቸው፣ በራሳቸው በመተማመናቸው የማይሸማቀቁባት፣ በሀገራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተካፋይ የሚሆኑባት፣ ሃሳባቸው የሚሰማባት እንድትሆን ሁላችንም እንትጋ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.