Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮችን እንግልት ለማስቀረት ወጥነት ያለው አሰራር መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮችን እንግልት ለማስቀረት ወጥነት ያለው አሰራር መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የህግ ባለሙያው አቶ ቡንካሾ ሃንጌ ተናግረዋል፡፡
ቅሬታቸውን ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ያቀረቡ የፍርድ ቤት ተገልጋዮች በየፍርድ ቤቱ ጉዳያቸው ያለአግባብ ተራዝሞ ላልተገባ ወጪ እና እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ መርምሮ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ የተለያዩ ችግሮችን በምክንያትነት በመጥቅስ ቀጠሮ እንደሚሰጡም ተገልጋዮች ጠቁመዋል፡፡
በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የህግ ባለሙያ ቡንካሾ ሃንጌ÷ ተገልጋዮች ውሳኔ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ፍርድ ቤት አቅርበው ፍትህን የማግኘት መብታቸው ሰብዓዊና ህገ መንግስታዊ ሆኖ በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ህግ ስር የተደነገገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ተገልጋዮች በፈጣን እና ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ ፍትህን እንዲያገኙ ህገ መንግስቱ ይደነግጋል ያሉት ባለሙያው÷ በተግባር የሚታየው ነገር ግን ፍትህ እየተራዘመ ባለጉዳዮችን ለአላስፈላጊ ወጪ እና መጉላላት የሚዳርግ፣ ፍትህንም የሚያዛባ ሆኖ ይገኛል ብለዋል፡፡
በጊዜ ገደብ ውስጥ አንድ ጉዳይ መፈፀም አለበት የሚል በህግ የተቀመጠ የጊዜ ጣራ አለመኖሩን ያነሱት አቶ ቦንካሾ÷ ነገር ግን የፍርድ ቤቶች አሰራር ወጥነት ማጣት ለችግሩ እንደ ዋነኛ ምክንያት ተጠቃሽ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
ከዚህ ውጪም በፍርድ ቤቶች ዘንድ ተገልጋይን ያለ ቀጠሮ ጉዳይን ተመላልሰው እንዲካታተሉ የማድረግ አሰራር መኖሩ ለባለጉዳይ መጉላላት ሌላው ምክንያት እንደሆነ ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቶች የአሰራር ስነስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ጊዜን በማብቃቃት በቀጠሮ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳዮችን ቅድሚያ እየሰጡ በማስተናገድ የባለ ጉዳዮችን መጉላላት ለማስቀረት መስራት ቢችሉ የተሻለ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በታምራት ቢሻው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.