Fana: At a Speed of Life!

5ኛው የተመድ አዳጊ ሀገራት ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 5ኛው የተባበሩት መንግሥታት አዳጊ ሀገራት ጉባኤ ከ “እምቅ አቅም ወደ ብልጽግና “በሚል መሪ ቃል በኳታር ዶሃ መካሄዱን ቀጥሏል፡፡

በየ10 ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ 46ቱ አዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ሽግግር በሚያመጡባቸው የድርጊት መርሐ ግብሮች ላይ ነው እየመከረ የሚገኘው።

ሀገራቱ ካሉባቸው ፈርጀ ብዙ ችግሮች ተላቀው ወደ ብልጽግና ለሚያደርጉት ጉዞ ካደጉ ሀገራት ምን ይጠበቃል እና ሀገራቱስ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራት ምን ምን ናቸው የሚሉ ጥያቄዎች በጉባኤው ተነስተዋል፡፡

ጉባኤው ከ10 ዓመታት በፊት በቱርክ ጸድቆ የነበረውን የኢስታንቡል መርሐ ግብር አፈጻጸምን ገምግሟል።

የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ለመርሐ ግብሩ አፈጻጸም ተግዳሮት ከነበሩት መካከል ዋነኛው መሆኑ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

ለቀጣይ አስርት ዓመታት ለሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ሊከናወኑ በሚገቡ ጉዳዮች ላይም ውይይት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዶሃው የድርጊት መርሐ ግብር የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ይጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ከ2022 እስከ 2031 የሚቆየው መርሐ ግብሩ ድህነትን መቀነስ፣ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የቴክኖሎጂ ሃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማመቻቸትና ወደ ብልጽግና የሚወስዱ መዋቅራዊ ለውጦችን መደገፍ የመርሐ ግብሩ ዓበይት ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ሀገራቱ በዓለም አቀፍ ንግድ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ፣ ኮቪድ -19 በምጣኔ ሃብታቸው ላይ ያደረሰውን ጫና እንዲቋቋሙ ማስቻል እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር የድርጊት መርሐ ግብሩ ዋነኛ ነጥቦች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በዳዊት አለሙ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.