Fana: At a Speed of Life!

የሸገር ከተማ አስተዳደደር በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሸገር ከተማ አስተዳደደር በአዲስ ባዋቀራቸው ክፍለ ከተሞች በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት መዋቅር ያልነበራቸው አዳዲስ ሰባት ክፍለ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ በአዲስ እንዲዋቀሩ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።

በአዲስ የተዋቀሩ ክፍለ ከተሞችን እና እንደገና እንዲደራጁ የተደረጉትን ጨምሮ 12 ክፍለ ከተሞች ለዜጎች በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጡትን አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰው ኃይልን በሚመለከት በአዲስ በተደራጁ ክፍለ ከተሞች በመልካም ስነ ምግባር እና ማህበረሰቡን በፍትሃዊነት ያገለግላሉ ተብለው የተለዩ አመራሮች መመደባቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ሰራተኞችን ከነባር ክፍለ ከተማ በማሸጋሸግ እንዲሁም በአዲስ ቅጥር በመፈጸም እንዲመደቡ መደረጉንም ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ክፍለ ከተሞች ስር የተዋቀሩ 33 ወረዳዎችንም በማደራጀት ወደስራ ለማስገባት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው አክለዋል።

አያይዘውም የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የመሬት ምዝገባ ስራን በቅርቡ እንደሚጀምርም ነው የተናገሩት።

ሰፊ የአርሶ አደር ማህበረሰብ የሚገኝበት ከተማ እንደመሆኑ መጠን ነዋሪውን በሚመጥን መልኩ አገልግሎት በመስጠት፥ የልማት ጥያቄዎችን በመፍታት ለወጣቱ በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድሎች መፍጠር የሸገር ከተማ አስተዳደር ዋናው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አስረድተዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የለገዳዲ ጣፎ ክፍለ ከተማ እና ሰንዳፋ መንገድ ገበረ ሚዛን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውና በአዲስ የተዋቀረውን የኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ ስራ መጀመራቸውን በቅኝት ተመልክቷል።

በኩራ ጂዳ ክፍለ ከተማ በዚህ በተጀመረ ስራ 105 ሔክታር መሬት ወደ ህጋዊ ስርዓት እንዲይዝ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደር ነዋሪዎች ክፍለ ከተሞቹ በአዲስ ተዋቅረው ስራ መጀመራቸው እንዳስደሰታቸው እና በአቅራቢያቸው ጊዜያቸውን በመቆጠብ አገልግሎት ማግኘት እንደሚያስችላቸው ነው የሚናገሩት።

ወጣቶች በበኩላቸው የሸገር ከተማ ተቋቁሞ ክፍለ ከተሞች በአዲስ መደራጀታቸውና ስራ መጀመራቸው የልማት ተጠቃሚ ያልሆኑ አካባቢዎች እንዲለሙ በማድረግ እና ለወጣቱ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ከፍ ያለ ሚና እንደሚኖረው አስተያየት ሰጥተዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.