Fana: At a Speed of Life!

በጌዴኦ ዞን 28 ሺህ ሄክታር መሬት በአፈር አሲዳማነት መጠቃቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ከሚታረሰው 123 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ  28 ሺህ ሄክታር መሬት በአፈር አሲዳማነት መጠቃቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡

የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ ዝናቡ ወልዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በዞኑ አጠቃላይ ከሚታረሰው 123 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 28 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሆነው በአፈር አሲዳማነት ተጠቅቷል፡፡

የአፈር አሲዳማነት ለሰብል ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ሲጨመሩ ችግሩ እንደሚከሰት ጠቅሰው÷ ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስና  ለመከላከል ባህላዊና ዘመናዊ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በጌዴኦ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በበጋ መስኖ ስንዴ ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች÷ የተለያዩ ሰብሎችን እያመረቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጅ በመሬቱ አሲዳማነት ምክንያት የምርትና ምርታማነት መቀነስ እያጋጠማቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ በፊት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራ ሰርተው እንደማያውቁ በመጥቀስም፥ መሬቱ በአሲዳማነት የተጠቃ ቢሆንም የተለያዩ ዜዴዎችን እየተጠቀሙ ሰብል እያመረቱ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።

በዞኑ ያለው መሬት በአሲዳማነት በመጠቃቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ ምርት ለመግባት ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ነውም ተብሏል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.