Fana: At a Speed of Life!

የቦረና ዞንን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የቦረና ዞንን የውሃ ችግር ለመቅረፍ በ5 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የተለያዩ የውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷ በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የተፈጠረውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ 41 የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡

ለዚህ ማስፈጸሚያም ከዓለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከኢጋድ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱን ጠቁመው÷ የዞኑን የውሃ ችግር በሁለት ዓመታት ውስጥ ለመፍታት በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

በዞኑ ከ16 ዓመት በፊት ተጀምሮ የነበረው እና አምስት ወረዳዎችን የሚያገናኘው የቦረና ውሃ ኔትወርክ ፕሮጀክት ቢጓተትም÷ ፕሮጀክቱ እየተገነባ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ከነበሩ 522 የውሃ ጉድጓዶች መካከል 119 ያህሉ በድርቁ ምክንያት አገልግሎት ማቆማቸውን የቦረና ዞን ውሃ እና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ይህም በዞኑ የነበረውን የውሃ ሽፋን ከ50 ነጥብ 7 ወደ 33 በመቶ እንዲወርድ ማድረጉን ነው የገለጸው፡፡

በአልማዝ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.